ስራና ደመወዝን

This page was last updated on: 2025-06-22

አነስተኛ የክፍያ ወለል

ብሔራዊ የሆነ አነስተኛ የክፍያ ወለል የለም፡፡ አነስተኛ ክፍያ ያለው በመንግስት ዘርፍ ብቻ ሲሆን ይህም 4760 ብር /36.20 የአሜሪካን ዶላር/ አካባቢ ነው ፡፡ አንዳንድ መንግስታዊ ተቋማት የራሳቸውን አነስተኛ የክፍያ መጠን ያስቀምጣሉ፡፡

በአዲሱ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የደመወዝ ቦርድን ስልጣንና ሃላፊነት ደንብ ሲያወጣለት: ቦርዱ ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያን ይመለከታል። የደመወዝ ቦርድ የመንግሥት፤ የአሠሪና ሠራተኛ ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያካትታል፡፡ የደመወዝ ቦርድ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት፤ የሥራ ገበያ ሁኔታ እና የመሳሰሉትን እያስጠና ዝቅተኛ ደመወዝ በየጊዜው ይከልሳል፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች መነሻ የደመወዝ ወለል የተወሰነው በብሔራዊ ደረጃ ሆኖ በሠራተኛ አገልግሎት ዓይነትና በሙያ ደረጃ ነው፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ላይ ተመሥርቶ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሲቭል ሠርቪስ ሚኒስቴር እንደገለፀው የመነሻ ደመወዝ ወለል ከሌሎች የደመወዝ ደረጃዎች ጋር እንደ ሠራተኛው የሙያና የአገልግሎት ዓይነት የሚከፈል ነው፡፡ የመነሻ ደመወዝ ወለል የሚሰላውም በቀን፣ በሰዓት፣ በሳምንት እና በወር ነው፡፡

የሠራተኛ እና ክህሎቶች ሚኒስቴር (MOLS) ለሠራተኛ ቁጥጥር እና የሠራተኛ ሕጎችን መከበራቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት። ሰራተኞች በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የሰራተኛ ቢሮ ቅሬታ ማቅረብ ይችላሉ።

ምንጭ፡ የአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2019 አንቀጽ 55(2)

አሁን ስራ ላይ ያለው አነስተኛ የክፍያ ወለል በአነስተኛ ክፍያ መደብ ስር ይገኛል፡፡

መደበኛ ክፍያ

በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ መሰረት ክፍያ ማለት ሰራተኛው/ዋ በስራ ቅጥር ውሉ መሰረት ለሚሰራው/ለምትሰራው ማግኘት ያለበት/ባት መደበኛ ክፍያ ነው፡፡ ክፍያዎች ከትርፍ ሰዓት ማካካሻ፣ አበሎች፣ ጉርሻ፣ ኮሚሽኖች፣ ከደንበኞች ከሚሰጥ የአገልግሎት ክፍያ እና ለተጨማሪ ስራ ከሚከፈሉ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ውጪ ናቸው፡፡ ክፍያዎች በአሰሪው አማካኝነት ተቋርጦ ስራ መስራት የማይቻል (ማለትም ቁሳቁሶች እና ጥሬ እቃዎችን ማቅረብ በማቆሙ) ካልሆነ በስተቀር ክፍያዎች ሰራተኛው/ዋ ለሰራው/ችው ስራ ብቻ የሚከፈሉ ናቸው፡፡ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ፡ አሠሪዎች የተለየ ስምምነት ከላደረጉ በስተቀር፡ ደሞዝ በስራ ቀንና በስራ ቦታ በጥሬ ገንዘብ እንዲከፍሉ ያስገድዳል። የመክፈያ ቀን (ቀድሞውኑ የተወሰነበት ካልሆነ ስተቀር)፡ በየሳምንቱ የእረፍት ቀን ወይም በህዝባዊ በዓል ላይ የሚውል ከሆነ፣ ደመወዙ የሚከፈለው ከሳምንቱ የእረፍት ቀን ወይም ከበአሉ በፊት ባለው የስራ ቀን ነው። ደመወዝ የሚከፈለው በቀጥታ ለሠራተኛው ወይም በሠራተኛው ለተፈቀደለት ሰው ነው። ደሞዝ በአይነት ሊከፈል ይችላል፤ ነገር ግን በጥሬ ገንዘብ ከሚከፈለው ደሞዝ ከ30% በላይ መብለጥ የለበትም።

አሰሪው ለሠራተኛው ደመወዙንና ሌሎች ክፍያዎችን በዚህ አዋጅ ወይም በህብረት ስምምነት መሠረት የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ የደመወዝ ክፍያ የሚፈፀምበት ጊዜ በህግ፣ በህብረት ስምምነት፣ በስራ ደንብ ወይም በስራ ውል በተወሰነው መሰረት ይሆናል፡፡

በአጠቃላይ አሰሪው በህጉ ወይም በህብረት ስምምነት ወይም በስራ ደንቦች ካልተደነገገ ወይም በፍርድ ቤት ትእዛዝ ወይም በሰራተኛው የጽሑፍ ስምምነት ካልሆነ በስተቀር ክፍያዎችን መቀነስ/መቁረጥ አይችልም፡፡ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የሚቀነስበት ከሆም: የሚቀነሰውም መጠን ሰራተኛው በየወሩ ከሚከፈለው ክፍያ 1/3ኛ መብለጥ የለበትም፡፡ አሰሪው የሰራተኛው ፊርማ ያለበት ልዩ ስምምነት ከሌለ በስተቀር በመዝገቡ ውስጥ ያልተጣራ ክፍያ፣ የክፍያዎችን ስሌት ዘዴ፣ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች፣ የተቀናሽ መጠን እና አይነት እና የተጣራ ክፍያ እና ሌሎች አግባብነት ያላቸው መግለጫዎችን የሚያሳይ የክፍያ መዝገብ የመያዝ ግዴታ አለበት፡፡ እንዲህ አይነቱ መዝገብ ለሁሉም ሰራተኞች ተደራሽ መሆን እና ሰራተኛው ጥያቄ ሲያቀርብ አሰራሩ/ስሌቱ ይብራራለታል፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለ13ኛ ወይም ለ14ኛ ወር ደመወዝ ወይም ለሌላ የግዴታ ጉርሻ ምንም አይነት ህጋዊ መስፈርት የለም። እነዚህ ክፍያዎች በድርጅቱ የሥራ ሕግ ወይም በጋራ ስምምነት መሠረት ሊደረጉ ይችላሉ::

የኢትዮጵያ መንግስት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 2011 ዓ.ም የፀደቀውን አዲሱን የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 (1156/2019) ነሄሴ 30 2011 ዓ.ም አሳትሟል፡፡ አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 (1156/2019): የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጆችን ቁጥር 377/1996፣ 466/1997፣ 494/1998 እና የሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 632/2001 ይሽራል፡፡

ምንጭ፡ የአሰሪ እና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2019 አንቀጽ 53-60

ስራና ደመወዝን የተመለከቱ ደንቦች

  • የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁ. 1156/2011 / Labour Proclamation No. 1156/2019
loading...
Loading...