This page was last updated on:
2025-06-22
ጎጂ ሥራዎች
የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ ሴቶች ከባድ ወይም ለጤናቸው ጎጂ ናቸው ተብለው ሚኒስቴሩ በሚዘረዝራቸው ሥራዎች ላይ ማሰማራትን /ነፍሰጡሮች ቢሆኑም ባይሆኑም/ ይከለክላል፡፡
በተመሣሣይም ነፍሰ ጡር ሰራተኞች ትርፍ ሰዓት ወይም የምሽት ስራዎችን እንዲሰሩ ሊጠየቁ አይችሉም፡፡ ነፍሰጡር የሆነች ሰራተኛ የምትሰራው ስራ ለራሷ ጤንነትም ሆነ ለፅንሷ አደገኛ ከሆነ ወደ ሌላ የስራ ቦታ ተመድባ መስራት አለባት፡፡
ምንጭ፡- የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2019 አንቀጽ 87
ከስራ ከመባረር ጥበቃ
ማንኛውም አሰሪ ሴት ሰራተኛ ነፍሰጡር በሆነችበት ጊዜና ከወለደችበት ቀን ጀምሮ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ከስራ ሊያሰናብት አይችልም፡፡ የሰራተኛ እርግዝና የሰራተኛዋን የስራ ውል ለማቋረጥ ምክንያት አይሆንም ነገር ግን ሴት ሰራተኛ ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር ባልተያያዙ ምክንያቶች ልትሰናበት ትችላለች፡፡
ምንጭ፡ በ 1994 በወጣው የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት አንቀጽ 35(5)፣ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2019 አንቀጽ 26(2) እና 87(5)
ቀድሞ ወደ ሥራ መደብ የመመለስ መብት
በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2019 ዓ.ም. ውስጥ ሴት ሠራተኛ ከወሊድ ፈቃድ በኋላ ወደነበረችበት የሥራ መደብ ትመለሳለች የሚል ቀጥተኛ የህግ አንቀጽ ባይኖርም በተዘዋዋሪ ግን አሠሪዋ በወሊድ ፈቃድ ምክንያት የሥራ ውል ማቋረጥ ስለማይችል በሥራ ውሉ መሠረት ወደነበረችበት የሥራ ኃላፊነት ወይም መደብ ይመልሳታል፡፡