የስራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳ

This page was last updated on: 2023-05-06

የስራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳ

የወንጀል ህግ የፆታ ትንኰሣን ይከለክላል፡፡ የፆታ ትንኰሣ ድርጊት የፈፀመን ሰው በቀላል እሥራት እንደሚቀጣ ይገልፃል፡፡ በወንጀል ህግ አንቀጽ 625 እንደተደነገገው አንድን ሴት ያለባትን ከፍ ያለ ችግር ወይም ጥገኝነትዋን ምክንያት በማድረግ ወይም በጠባቂነት፣ በአስተማሪነት፣ በአሳዳሪነት፣ በአሠሪነት ወይም ይህን በመሠለ በማናቸውም ግንኙነት ምክንያት ያገኘውን ሥልጣን፣ ኃላፊነት ወይም ችሎታ በመጠቀም በማንኛውም ሴት ላይ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት የፈፀመ ወይም የግብረ-ሥጋ ግንኙነት የመሠለ ድርጊት ወይም ለንጽህና ክብር ተቃራኒ የሆነ ማናቸውንም ሌላ ዓይነት ድርጊት የፈፀመ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት በቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡

ለማናቸውም አሠሪ ወይም የስራ ሃላፊ በሥራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት መፈፀም ህገወጥ ድርጊት ነው፡፡ በተመሳሳይ ሰራተኞች በሥራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት መፈፀም የለባቸውም፡፡ ወሲባዊ ትንኮሳ ማለት በንግግር፣ በምልክት ወይም በሌላ ማናቸውም አድራጎት አንዱ ሌላውን ከፈቃዱ ውጭ ለወሲባዊ ተግባር ፈቃደኛ እንዲሆን ማባበል፣ መገፋፋት፣ ተፅዕኖ ማሳደር ነው፡፡ ወሲባዊ ጥቃት ማለት ኃይል የተቀላቀለበት ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም የዚሁ ድርጊት ሙከራ ነው፡፡

ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት የደረሰባቸው ሠራተኞች የሥራ ውላቸውን ያለ ማስጠንቀቂያ ማቋረጥ ይችላሉ እንዲሁም የሥራ ስንብት ክፍያ እና ካሣም ያገኛሉ፡፡ የተሻሻለው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ በወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት ምክንያት የሥራ ውላቸውን ያለ ማስጠንቀቂያ እንዲያቋርጡ ለሚገደዱ ሰራተኞች ከፍተኛ የካሣ ክፍያን ይደነግጋል፡፡ በወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት ምክንያት የሥራ ውልን ያለ ማስጠንቀቂያ ማቋረጥ የ 3 ወር የካሳ ክፍያን ያስከትላል፡፡

ምንጭ፡-የወንጀለኛ መቅጫ አዋጅ ቁጥር 141/1996 አንቀፅ 89(2)፤የተሻሻለው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀፅ 14

loading...
Loading...