የማስታወቂያ አስፈላጊነት - የስራ ስንብት ክፍያ

This page was last updated on: 2025-06-22

የማስታወቂያ አስፈላጊነት

በህጉ ወይም ህብረት ስምምነት ወይም በሁለቱ ተዋዋይ ወገኖች ስምምነት መሰረት ማንኛውም ወገን ማስታወቂያ በመስጠት ወይም አስፈላጊውን ክፍያ በመፈፀም ውሉን ሊያቋርጥ ይችላል፡፡ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ መሰረት ለተወሰነ ጊዜ ወይም ስራ የተገባው የስራ ውል ሲያበቃ ወይም ሲጠናቀቅ፣ ሰራተኛው ሲሞት ወይም ሰራተኛው በህጋዊ መንገድ ጡረታ ሲወጣ ድርጅቱ በኪሳራ ወይም በሌላ ማንኛውም ምክንያት ሙሉ በሙሉ ስራ ሲያቆም ወይም በአካል ጉዳት ምክንያት መስራት የማይችል ሲሆን የስራ ቅጥር ውሉ ሊቋረጥ ይችላል፡፡ እንዲሁም የስራ ቅጥር ውሉ ከሰራተኛው ጠባይ ወይም የሠራተኛውን የመስራት ችሎታ ወይም ከድርጅቱ ድርጅታዊ አቋም ወይም የስራ እንቅስቃሴ ጋር ባላቸው ምክንያቶች ሊቋረጥ ይችላል፡፡ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ በተጨማም የስራ ውል ያለማስጠንቀቂያ ሊቋረጥ የሚችልባቸውን ሁኔታዎች ይጠቅሳል፡፡ ውሉን ማቋረጥ የፈለገ ሰራተኛ ለአሰሪው የ30 ቀናት ቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ማቋረጥ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል አሰሪው ከሰራተኛው ጋር ያለውን የስራ ውል ማቋረጥ ከፈለገ ማስታወቂያ የሚሰጠው በሚከተለው መሰረት ይሆናል፡፡ - አንድ ወር፡ የሙከራ ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ ሰራተኞች እና የአገልግሎት ጊዜያቸው ከ 1 ዓመት ላልበለጠ - ሁለት ወር፡ ከአንድ እስከ ዘጠኝ (1-9) ዓመታት የአገልግሎት ጊዜ ላላቸው ሠራተኞች - ሦስት ወር፡ ከ 9 ዓመት በላይ አገልግሎት ላላቸው ሠራተኞች፣ እና - ሁለት ወር፡ የሙከራ ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ ነገር ግን በሠራተኛ ኃይል ቅነሳ ምክንያት ሥራቸው ለተቋረጠ ሠራተኞች።

ለተወሰነ ጊዜ ወይም ለተወሰነ ሥራ የተደረገ የሥራ ውልን በሚመለከት የማስጠንቀቂያ ጊዜው ተዋዋይ ወገኖች በውሉ ላይ በተስማሙት መሠረት ይሆናል፡፡ ከላይ የተገለጹት የስታንዳርድ ማስታወቂያ ጊዜዎች በሙከራ ጊዜ ውስጥ ከሥራ ማባረር ፣የውስን ጊዜ ውል ሲያልቅ እና ሠራተኛን በከባድ የስነ ምግባር ጉድለት ምክንያት ከሥራ ማሰናበት ሲከሰት ተፈፃሚ አይሆንም።

ምንጭ፡- የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2019 አንቀፅ 24-35፣ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2571፣ የ 1960 አዋጅ ቁጥር 165::

የስራ ስንብት ክፍያ

የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ የሙከራ ጊዜውን ላጠናቀቀ አንድ ሰራተኛ የስራ ስንብት ክፍያ እንደሚከፈለው ይደነግጋል፡፡ የስራ ቅጥር ውሉ የአሰሪው ድርጅት በቋሚነት ስራዎቹን በኪሳራ ወይም በሌላ ምክንያት በማቆሙ በአሰሪው የተቋረጠ እንደሆነ ወይም የሰራተኛው የስራ ቅጥር ውል ከህግ ድንጋጌ ውጪ ከተቋረጠ ወይም ሰራተኛው የተቀነሱ ሰራተኞች ውስጥ ከተካተተ ወይም አሰሪው የሰራተኛውን መብት የሚነካ ህገ-ወጥ ድርጊት ከፈጸመ ወይም አሰሪው የሰራተኞችን ጤና እና ደህንነት ለመጠበቅ ስላለው አደጋ ሲነገረው ምንም አይነት የጥንቃቄ እርምጃ ካልወሰደ እና የስራ ቅጥር ውል ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የአካል ጉዳት ስለደረሰበት የሥራ ውሉ የተቋረጠ ሰራተኛ የስራ ስንብት ክፍያ የማግኘት መብት ይኖረዋል፡፡ ሠራተኛው በፈቃዱ ከሥራ ሲሰናበት፣ ሠራተኛው በከባድ ጥፋት ምክንያት ከሥራ ሲሰናበት እና የውስን ጊዜ ውል ሲያጠናቅቅ የሥራ ስንብት ክፍያ አይከፈልም። ሠራተኛው በፈቃዱ ከሥራ ሲሰናበት፣ ሠራተኛው በከባድ ጥፋት ምክንያት ከሥራ ሲሰናበት እና የውስን ጊዜ ውል ሲያጠናቅቅ የሥራ ስንብት ክፍያ አይከፈልም።

የስራ ስንብት ክፍያው መጠን በአገልግሎት ዘመን ላይም የተመሰረተ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በሚከተለው ተመን መሰረት የሚከፈል ይሆናል፡፡ - የ 30 ቀናት ደሞዝ ለአንድ አመት (እንዲሁም የመጀመሪያ አመት) አገልግሎት፡፡ (ከ 1 አመት በታች ለሆኑ ሰራተኞች የስንብት ክፍያ ከአገልግሎት ጊዜ ጋር በተመጣጣኝ መጠን ይሰላል)፣ - ከመጀመሪያው ዓመት በኋላ ለእያንዳንዱ ተጨማሪ የአገልግሎት ዓመት የ 10 ቀናት ደመወዝ፡፡ (ነገር ግን አጠቃላይ የሥራ ስንብት ክፍያ ከ 12 ወር ደመወዝ መብለጥ የለበትም)፣ - ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት ክፍያዎች በተጨማሪ: የ60 ቀናት ደሞዝ በቅናሽ ምክንያት ለተቋረጡ ሰራተኞች

ከላይ ከተመለከተው የሥራ ስንብት ክፍያ በተጨማሪ ሠራተኞች ያለማስጠንቀቂያ የሥራ ውላቸውን ሲያቋርጡ ተጨማሪ የ30 ቀናት ክፍያ በካሣ መልክ ያገኛሉ፡፡ የሥራ ውልን ያለ ማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ በቂ ምክንያቶች ዝርዝር የሚከተሉትን ሁኔታዎች ያካትታል፡- አሠሪው የሠራተኛውን ሰብአዊ ክብርና ሞራል የሚነካ ወይም በወንጀል ሕጉ መሠረት የሚያስቀጣ ሌላ አድራጎት የፈጸመበት እንደሆነ፤ ለሠራተኛው ደኅንነት ወይም ጤንነት የሚያሰጋና ሊደርስ የተቃረበ አደጋ የኖረ እንደሆነ፤ አሠሪው አደጋን እንዲቀርፍ እና ለመከላከል በሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ እርምጃዎችን ያልወሰደ እንደሆነ እና በዚህ አዋጅ በኅብረት ስምምነት ወይም በሥራ ደንብ ወይም አግባብ ባላቸው ሌሎች ሕጎች በተወሰነው መሠረት አሠሪው ለሠራተኛው መፈጸም ያለበትን ግዴታዎች በመደጋገም ያልፈጸመ እንደሆነ፡፡

አንድ ሰራተኛ በአሠሪ ወይም በሥራ መሪ በሚፈፀምበት ወሲባዊ ጥቃት ወይም ትንኮሳ ምክንያት የሥራ ውሉን ያለማስጠንቀቂያ ያቋረጠ እንደሆነ ሰራተኛው ከሥራ ስንብት ክፍያው በተጨማሪ የቀን ደመወዙ በ90 ተባዝቶ ይከፈለዋል፡፡

ምንጭ፡- የተሻሻለው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2019 አንቀፅ 32፣39-40

loading...
Loading...