በሒፋም ሰኢድ አሊ ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ እና በሒፋም ሰኢድ አሊ ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ መሠረታዊ ሠራተኞች ማህበር

Untitled Document

መካከል የተደረገ አንደኛው ህብረት ስምምነት

ድርጅቱን እና መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበሩን በመወከል ይህን አንደኛውን የህብረት ስምምነት ድርድር ያደረጉ የኮሚቴ አባላት፡-

ድርጅቱን በመወከል፡-

  1. አቶ ቢኒያም መኮነን ተሾመ
  2. አቶ አብዱ እብራሂም መሀመድ
  3. አቶ መሀመድ የሱፍ መለስ

ሠራተኛ ማህበሩን በመወከል

  1. ወ/ሮ/ሪት መሊካ ሀሰን አህመድ
  2. አቶ አወል ይመር መሀመድ
  3. ወ/ሮ/ሪት ተምር ጀማል አደም

የህብረት ስምምነቱ ዓላማ

የህብረት ስምምነቱ ዋና ዓላማ የስራ ሁኔታዎችንና የስራ ግንኙነቶችን በመወሰን ፣ ችግሮች ሲከሰቱ ተወያይቶ ለመፍታት የሚያስችል ሁኔታ በመፍጠር ፣ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት ፣ የድርጅቱ እና የሠራተኞች መብት እንዲከበሩ በማድረግ በአጠቃላይ በድርጅቱና በሠራተኛው መካከል መልካም ግንኙነትን በመፍጠር የኢንዱስትሪ ሰላም ለማስፈን ነው፡፡

አንቀጽ አንድ

አጭር ርዕስ

ይህ ህብረት ስምምነት በሒፋም/ሰኢድ አሊ ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ እና በሒፋም/ሰኢድ አሊ ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ መሰረታዊ የሠራተኞች ማህበር ጋር የተደረገ አንደኛው ህብረት ስምምነት ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

አንቀጽ ሁለት

ትርጉም

የቃሉ አግባብ ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው በስተቀር በዚህ ህብረት ስምምነት ውስጥ፡-

2.1 “አዋጅ” ማለት የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ማለት ነው፡፡

2.2 “ህጉች ደንቦች መመሪያዎች” ማለት መንግስት ያወጣቸውንና ወደፊትም የሚያወጣቸውን መመሪያዎች፣ ደንቦችና ህጎች ድርጅቱ የሚያወጣው ደንብ፣ የስራ መመሪያና ህብረት ስምምነት ጨምሮ ማለት ነው፡፡

2.3 “ድርጅት” ማለት የሒፋም/ሰኢድ አሊ ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ ማለት ነው፡፡

2.4 “አሰሪ” ማለት በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 2 ተራ ቁጥር 1 የተሰጠ ትርጉም ነው፡፡

2.5 “ሠራተኛ ማህበር” በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሰረት የተቋቋመና ከሚመለከተው የመንግስት መስሪያ ቤት ህጋዊ እውቅና ያገኘ የሒፋም/ሰኢድ አሊ ፒፒ ከሪጢት ፋብሪካ መሰረታዊ የሠራተኞች ማህበር ማለት ነው፡፡

2.6 “የድርጅቱ ማኔጅመንት ወይም የስራ መሪ” ማለት በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 አንቀጽ 2 ተ.ቁ 10 በተገለጸው መሰረት ሆኖ በቀጣይ በድርጅቱ በሚዘጋጅ ወይም በስራ ላይ በሚገኝ አደረጃጀት መሰረት በስራ መሪ ደረጃ የሚካተቱ የስራ ኃላፊዎች ማለት ነው፡፡

2.7 “ሠራተኛ” ማለት በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 4 በተመለከተው መሰረት ከሒፋም /ሰኢድ አሊ ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ ጋር በቅጥር ላይ የተመሰረተ የሥራ ግንኙነት ያለው ግለሰብ ነው፡፡

2.8 “ደመወዝ” ማለት አንድ ሰራተኛ በስራ ውሉ መሰረት ለሚከናውነው ሥራ የሚከፈለው መደበኛ ክፍያ ነው፡፡ ስለ ሌሎች ክፍያዎች በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 53 ተራ ቁጥር 2 መሰረት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

2.9 “የወር ደመወዝ” ማለት ለወር ተካፋዮች በ26 ቀናት በሥራ ውሉ መሰረት ላከናወኑት ሥራ ተተምኖ የሚደረግ ክፍያ ነው፡፡

2.10 “የህብረት ስምምነት” ማለት የሒፋም/ሰኢድ አሊ ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ እና የሒፋም/ሰይድ አሊ ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ መሠረታዊ የሠራተኞች ማህበር መካከል የተደረገ የህብረት ስምምነት ማለት ነው፡፡

2.11 “የሥራ ክርክር” ማለት ህግን ፣ የህብረት ስምምነትን ፣ የሥራ ደንብን ፣ የስራ ውልን ወይም ሲሰራበት የቆየ ልምድን መሰረት በማድረግ እንዲሁም በህብረት ስምምነት ድርድር ወቅት ወይም ከህብረት ስምምነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሚመለከት በሰራተኛና በአሰሪ ወይም በሰራተኞች ማህበርና በአሰሪዎች መካከከል የሚነሳ ክርክር ነው፡፡

2.12 “ዋና ስራ አስኪያጅ/ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ” ማለት የሒፋም/ሰይድ አሊ ፒፒ ከሪጢት ፋብሪካን ተረክቦ እንዲመራ የተመደበ የበላይ ኃላፊ ማለት ነው፡፡

2.13 “የሠራተኛ ማህበር መሪዎች” ማለት የሰራተኛ ማህበሩን ለመምራት በጠቅላላ አባል ሠራተኞች የተመረጡ የሥራ አስፈፃሚ እና የኦዲት ኮሚቴ አባላት ማለት ነው፡፡

2.14 “የሠራተኛ ማህበር የምክር ቤት አባል” ማለት የሠራተኛ ማህበሩ አባል ሆነው በሥራ ክፍሎቹ የተወከሉ እና በሠራተኛ ማህበሩ ወቅታዊ ስብሰባዎች ላይ የሚሳተፉ አባላት ማለት ነው፡፡

2.15 “መዋቅር” ማለት በባለሙያ ተጠንቶ በስራ ላይ የዋለ የድርጅቱ አደረጃጀት ሲሆን ፣ የሰው ኃይል ዕቅድ ፣ ደመወዝ ፣ የሥራ መደብን ፣ የደረጃ መስፈርቶች የያዘ ሰነድ ማለት ነው፡፡

2.16 “የስራ ደንብ” ማለት በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 እና በሌሎች አግባብ ባላቸው ህጎች የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ የስራ ሰአትን ፣ የዕረፍት ጊዜን ፣ የደመወዝ አከፋፈልንና የስራ አፈጻጸም ውጤት መለኪያ ዘዴን ፣ የደህንነት ጥበቃንና የአደጋ መከላከያን የዲስፕሊን ደንቦችንና አፈጻጸማቸውን እንዲሁም ስለሌሎች ደንቦችንና አፈጻጸማቸውን የሚደነግግ የውስጥ ደንብ ነው፡፡

2.17 “የስራ ሁኔታ” ማለት በአሠሪና ሠራተኞች መካከል ያለ ጠቅላላ ግንኙነት ሲሆን ይህም የስራ ሰአትን ፣ ደመወዝን ፣ ፈቃዶችን ሠራተኞች ከስራ በሚሰናበቱበት ጊዜ የሚገባቸውን ክፍያዎች ፣ ጤንነትና ደህንነት በስራ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ሠራተኞች የሚከፈል ካሳ ፣ ሠራተኞች ከስራ የሚቀነሱበትን ሁኔታ ፣ የቅሬታ አቀራረብ ስርአቶችንና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡

2.18 “ወሲባዊ ትንኮሳ” ማለት በንግግር ፣ በምልክት ወይም በሌላ ማናቸውም አድራጎት አንዱ ሌላውን ከፈቃዱ ውጭ ለወሲባዊ ተግባር ፈቃደኛ እንዲሆን ማባባል ፣ መገፋፋት ፣ ተፅዕኖ ማሳደር ነው፡፡

2.19 “ወሲባዊ ጥቃት” ማለት ኃይል የተቀላቀለበት ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም የዚሁ ድርጊት ሙከራ ነው፡፡

2.20 “ህመም ” ማለት ከስራ ጋር ግንኙነት በሌለው ምክንያት የሚመጣ የጤና መታወክ ማለት ነው፡፡

2.21 “የስራ ላይ አደጋ ” ማለት ስለአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 97 ከተራ ቁጥር 1 እስከ 4 የተዘረዘሩትን የሚያካትት ነው፡፡

2.22 “ደረጃ ዕድገት” ማለት አንድ ሠራተኛ በድርጅቱ የሥራ መደቦች ከነበረበት የስራ መደብ ከፍ ወዳለ የስራ መደብ ከሙሉ መብቱና ኃላፊነቱ ጋር የሚደረግ ምደባ ነው፡፡

2.23 “የደረጃ ዝቅታ ” ማለት በድርጅቱ የሥራ መደቦች ደረጃ ከነበረበት የሥራ መደብ ዝቅ ወዳለ የሥራ መደብ የሚደረግ የሥራ ምደባ ነው፡፡

2.24 “ዝውውር ” ማለት በድርጅቱ መዋቅር መሠረት በተመሳሳይ ደረጃና ደመወዝ አዛውሮ ማሰራት ማለት ነው፡፡

2.25 “ቅሬታ” ማለት ሠራተኛው በዚህ መመሪያ መሰረት በድርጅቱ የተፈፀመበትን/የተወሰነበትን ጉዳይ በመቃወም የሚያቀርበው አቤቱታ ነው፡፡

2.26 በዚህ ህብረት ስምምነት በማንኛውም የወንድ ጾታ የተገለጸ የሴትንም ጾታ ይጨምራል፡፡

አንቀጽ ሶስት

መብትን ስለማወቅ

3.1 መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበርን ስለማወቅ

3.1.1 አሠሪው የሠራተኛ ማህበሩን ሥለማናቸውም የሥራ ሁኔታዎች የህብረት ስምምነት ክርክር የሠራተኛ ተወካይ መሆኑን አውቆ ይቀጥላል፡፡

3.1.2 አሰሪው በህግ ከታወቀው ሠራተኛ ማህበር ሌላ በግልም ሆነ በቡድን በህጋዊ መንገድ በመደራጀት መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በህግ ወጥ መንገድ የማህበሩን ህልውና የሚቃረኑ ሰራተኞች አይደግፉም፣ አያበረታታም፣ አያስተናግድም ፣ እርምጃ ይወስዳል፡፡

3.2 ድርጅትን ስለማወቅ

3.2.1 ድርጅቱ ስራውን የመምራትና የማስተዳደር ስልጣን መሰረት ስራውን ለማቀድ ፣ለመምራትና ለመቆጣጠር ፣ የእያንዳንዱን ሠራተኛ ተግባርና ኃላፊነቱን ለመወሰን የስራ አፈጻጸሙን በመከታተል በህብረት ስምምነቱ መሰረት ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ሙሉ ስልጣን ያለው መሆኑን ፣

3.2.2 ስለአሠሪና ሠራተኛ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ 2(ሐ) መሰረት ምርታማነትን ለማሰደግ የአሰራር ዘይቤዎችን ለመለውጥ ወይም በአዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ፣ እንዲሁም ተወዳዳሪነትን በማጎልበት የድርጅቱን ህልውና በማስጠበቅ ትርፋማነትን ቀጣይ ለማድረግና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ፣

3.2.3 ስለአሠሪና ሠራተኛ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 29 (3) እና በዚህ ህብረት ስምምነት በተገለጸው መሰረት የሠራተኞች ቅነሳ ሲደረግ ከመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ጋር በመመካከር የሚያከናውን መሆኑን ፣

3.2.4 ድርጅቱ ከዚህ ህብረት ስምምነት ጋር የማይቃረኑ ግዴታዎችን ፣መብቶችን ፣ የስራ ሁኔታዎችን ፣ ፖሊሲዎችን ፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን ፣ለማውጣት ፣ ለመወሰንና ለመሰረዝና ስልጣን ያለው መሆኑን ፣

3.2.5 ድርጅቱ በአዋጅና በዚህ ህብረት ስምምነት መሰረት ሠራተኛ ለመቅጠር ፣ የማዛወር ፣ የደረጃ ዕድገት ለመስጠት ፣ ጥፋት ያጠፋ ሠራተኛን እንደጥፋቱ ደረጃ ተገቢውን የስነ ስርአት እርምጃ የመውሰድ ፣ስራው ህጋዊ በሆነ ምክንያት እንደማይቀጥል ሲረጋገጥ የሠራተኛውን የስራ ውል በህግ አግባብ ለማቋረጥ ስልጣን ያለው መሆኑን ማህበሩ አውቆለታል፡፡

አንቀጽ አራት

ስህተትን ስለማርም

ድርጅቱ በህብረት ስምምነት እና በሌሎች ተያያዥ ህጎች ያልተፈቀደ ወይም በስሌት ስህተት ለሠራተኛ የሥራ ደረጃ ፣ የደመወዝ እድገት ፣ ጭማሪ ፣ የዓመት ዕረፍት ቢሰጥ እንዲሁም ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን እና ይህንንም የመሳሰሉ ሌሎች ማንኛውም ስህተቶች ተፈፅመው ሲገኙ ስህተቱን በአንድ ዓመት ውስጥ ማረም ይችላሉ፡፡ ይህም፡-

ሀ. የደመወዝ ብልጫ ጭማሪ እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን የተሰጠው ሠራተኛ ደመወዙ ከተጨመረበት ቀን አንስቶ እስከተስተካከለበት ቀን ድረስ የተሰጠው ብልጫ በየወሩ የደመወዝ 1/3ኛ በማይበልጥ ሁኔታ ከደመወዙ ላይ እየተቀነሰ ገቢ ይሆናል፡፡

ለ. ማግኘት የነበረበት ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የተቀነሰበት ሠራተኛ ይስተካከልለትና ቀደም ብሎ ያልተከፈለው ተሰልቶ በአንድ ጊዜ ይከፈለዋል፡፡ ሆኖም ሌሎች የመብትና የክፍያ ስህተቶችን በተመለከተ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 እና አግባብ ባለው ህግ መሰረት ይታያል፡፡

ሐ. የደረጃ ዕድገት ምደባ በስህተት ለሠራተኛ ከተሰጠ በታወቀበት ጊዜ ያለአግባብ የተሰጠው ደረጃና ደመወዝ እንዲነሳ ይደረጋል፡፡ በስህተት ሳያገኝ የቀረው ከተመደበበት ቀን አንስቶ የሚገባውን ደረጃና ደመወዝ ይሰጠዋል፡፡ ስህተቱን የፈፀመው አካል ግን በህብረት ስምምነት ወይም በስራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ተገቢው አስተዳደራዊ እርምጃ ተጣርቶ የሚወሰድበት ይሆናል፡፡

አንቀጽ አምስት

የሠራተኛ ማህበሩ በድርጅቱ የስራ እንቅስቃሴዎች ላይ ስለሚካፈልበት ሁኔታ

5.1 ድርጅቱን ለማስፋፋት ፣ የተሻለ ምርትና የአስተዳደር መልክ ለመስጠት የድርጅቱን ተልዕኮ እና አላማ ለማስፈፀም በሚደረገው ጥረት ከአሰሪው ጋር በመመካከር ሃሳብ በማቅረብ ሠራተኛውን በማሳመን የበኩሉን ድርሻ ይወጣል፡፡

5.2 ድርጅቱ አጠቃላይ ሠራተኛውን የሚመለከት የውስጥ አሰራር ከመለወጡ ወይም ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በቅድሚያ ለማህበሩ ያሳውቃል፡፡

5.3 ሠራተኛ ማህበሩ የሠራተኛ ቅጥር ፣ ዕድገትና ዝውውር በሚታይበት ኮሚቴ ውስጥ አንድ አባል ያሳትፋል፡፡ በአንድ ጊዜ ከሁለት በላይ ፈተና የሚሰጥ ከሆነ ሠራተኛ ማህበሩ ከአንድ በላይ የስራ አስፈፃሚ ለመመድብ ይችላል፡፡ ሠራተኛ ማህበሩ የማይሳተፍበት ተጨባጭ ምክንያት ካቀረበ ድርጅቱ ቅጥር ፣ ዕድገትና ዝውወር ከመፈፀም አያግደውም፡፡

5.4 የሠራተኛውን ደህንነት ለመጠበቅና ሞራሉን ለመገንባት ድርጅቱ የሚያደርገው ጥረት ሁሉ የሠራተኛ ማህበሩ እንዲያውቀው ይደረጋል፡፡

5.5 ሠራተኛ ማህበሩ የስራ ሁኔታዎች ፣ የሠራተኛ ማህበሩን የሥራ እንቅስቃሴ ለመገምገም ፣ ሠራተኛውን ለመሰብሰብ ቢፈልግ አሰሪው በዓመት አንድ የሥራ ቀን ከሰራተኛ ማህበሩ ጋር በመመካር ይፈቅዳል፡፡

5.6 ሠራተኛ ማህበሩ በድርጅቱ እቅድና አፈፃፀም ግምገማ ላይ ይሳተፋል ፣ ገንቢ የሆኑ አማራጭ ሀሳቦችንም ይሰጣል፡፡

5.7 አደጋ የደረሰባቸው ሠራተኞች መግለጫ ድርጅቱ ለኢትዮጵያ መድን ሞልቶ የሚያሳውቅበትን የሪስክ ማኔጅመንት ካሳና ጥቅማ ጥቅም ቅጽ አንድ ኮፒ ለሠራተኛ ማህበሩ ይሰጣል፡፡

5.8 ጠቅላላ ሠራተኛ የሚመለከቱ ጥናቶችን እንዲሁም የሥራ ደንቦች ፣ መመሪያዎች ሲወጡ ድርጅቱ ለሠራተኛ ማህበሩ አንድ ኮፒ ይሰጣል፡:

አንቀጽ ስድስት

የድርጅቱ መብት

6.1 ድርጅቱ ስራ የመምራት ፣ የማቀድ ፣ የመቆጣጠር እንዲሁም በዚህ ህብረት ስምምነት በተጠቀሱ ጉዳዮች ላይ በመመርኮዝ ሠራተኞችን የመቅጠር ፣ በየቦታው የመመደብ ፣ የማሳደግና ከቦታ ቦታ ለማዘወዋር መብቱ የድርጅቱ ነው፡፡

6.2 በዚህ ህብረት ስምምነት መሰረት ጥፋተኛ የሆነ ሠራተኛ ላይ ጥፋተኝነቱ ሲረጋገጥ በበቂ ምክንያት አስተዳደራዊ እርምጃ የመውሰድ ፣ ከደረጃና ከደመወዝ ዝቅ የማድረግና ከዲሲፕሊን ጋር በተያያዘ ሁኔታ ጉዳዩ እስከሚጣራ ድረስ በሌላ ሥራ አዛውሮ ለማሰራት ወይም ማገድ ይችላል፡፡ ሆኖም ሠራተኛው አጥፊ ሆኖ ካልተገኘ የታገደበት ደመወዙ ተከፍሎት ወደቀድሞ ሥራው ይመለሳል፡፡

6.3 አዲስ የሥራ ቦታን የመክፈት ወይም የማጠፍ አስፈላጊነቱን የመወሰን ፣ በየስራ መደብ አስፈላጊውን የሰው ኃይል የመወሰን ፣ ሠራተኛን የማሳደግና የእርከን ጭማሪ የማድረግ ለየስራ መደቡ የሚያስፈልገውን የትምህርት ደረጃ ፣ የስራ ልምድ የማውጣት የመወሰን መብት የድርጅቱ ነው፡፡

6.4 ስለድርጅቱ የስራ ሁኔታ ፣ ኃብትና ንብረት አጠባበቅ ከሌላ ሦስተኛ ወገን ጋር የመነጋገር ፣ ስለዕቃ ግዥና ሽያጭ የመዋዋል ፣ ኢንሹራንስ የመግባት ፣ ሌላም ለድርጅቱ ስራ አስፈላጊ የሆነ ውል የመግባት በድርጅቱ ስም የመክሰስና የመከሰስ መብት አለው፡፡

6.5 በድርጅቱ አጠቃላይ የስራና የሠራተኛ ጉዳይን በሚመለከት ፣ በትምህርት ፕሮግራም ፣ በትርፍና ኪሳራ ወይም በማንኛውም ጉዳይ መግለጫ የመስጠትና ማስታወቂያ የማውጣት መብት አለው፡፡

6.6 ሠራተኛው ከድርጅቱ የተበደራቸውን ብድሮች ፣ የመንግስት ግብር ለመክፈል፣ በጽሁፍ የተስማማበትን ጉዳይ ወይም እንዲከፍል ከፍርድ ቤት የተወሰነበትን ገንዘብ ድርጅቱ ሠራተኛው ከሚያገኘው መደበኛ ወርሃዊ ደመወዝ ላይ ቀንሶ መስጠት ወይም ለህጋዊ ባለመብቶች የመክፈል መብት አለው፡፡

6.7 በአጥፊዎች ላይ ሊወሰዱ የሚገባቸውን የሥነ-ስርዓት እርምጃዎች በህጉ መሰረት የመወሰን ፣ የማሻሻል ፣ ቅጣቶችን የማንሳት ወይም ይቅርታ የማድረግ በዲስፒሊን ኮሚቴ ወይም በሰው ኃብት አስተዳደር እና ሠራተኛው በሚሰራበት የስራ ክፍል መነሻ ሀሳብ መሰረት በድርጅቱ የበላይ አካል የሚወሰን ነው፡፡ በዲስፒሊን ጥፋት ከስራ የተሰናበተን ሠራተኛ ይቅርታ ማድረግ የሚችለው የድርጅቱ የበላይ አካል ወይም ተወካይ ብቻ ነው፡፡

6.8 ሕግን ደንብና መመሪያን በመከተል የቅጥር ፣ የደረጃ ዕድገት ፣ የዝውውርና የትምህርት ሥልጠናና ሌሎች የሠራተኛውን እንቅስቃሴ የሚመለከት ምርት ፣ ጥገና ፣ ግዥና ሽያጭ ፣ የንብረት አጠባበቅና አጠቃቀም ፣ የፋይናንስና ሌሎች አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች መመሪያ የማውጣት ፣ የመስጠትና የማስፈፀም መብት አለው፡፡

6.9 ለድርጅቱና ለሠራተኛው ደህንነት እንዲሁም ለድርጅቱ ኃብትና ንብረት ጥበቃ ሲባል በመውጫና በመግቢያ በር ላይ ፍተሻ የማድረግ መብት አለው፡፡

6.10 በማንኛውም ሁኔታ ላይ የሌላውን ስብዕና የሚነካ ወይም ባልተጨበጠ መረጃ ሀሰተኛ መልዕክት ያስተላለፈ ወይም ሁከት እንዲፈጠር ያደረገ ሠራተኛን ተገቢው ማጣራት ተደርጎ በማስረጃ ሲረጋገጥ ድርጅቱ በዚህ ህብረት ስምምነት መሰረት አስተዳደራዊ እርምጃ የመውሰድና በህግ የመጠየቅ መብት አለው፡፡

አንቀጽ ሰባት

የድርጅቱ ግዴታ

7.1 በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅና በዚህ ህብረት ስምምነት ወይም በሌሎች የመንግስት ህጎች፣ መመሪያዎችና ደንቦች ላይ የተመለከቱትን መብቶችና ግዴታዎች በትክክል በስራ ላይ የማዋል ግዴታ አለበት፡፡

7.2 ድርጅቱ በብሄር ፣ በፆታ ፣ በኃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት በሠራተኛ መካከል ልዩነት አያደርግም፡፡

7.3 በስራ ውሉ መሰረት ሊከፈል የተስማማውን ደመወዝና ሌሎች ተከፋዮችን በተወሰነው ጊዜ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡

7.4 በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 12/1 ሀ እና ለ መሰረት ድርጅቱ ለስራ የሚያስፈልገውን መሳሪያ እና ጥሬ ዕቃዎች ለሠራተኞች የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡

7.5 ድርጅቱ በማንኛውም በሠራተኛ ላይ የሠራተኛ ማህበር መሪ ወይም አባል በመሆኑ እና ባለመሆኑ ተፅእኖ ወይም አድሎ አያደርግም፡፡

7.6 አንድ የሠራተኛ ማህበር መሪ በማህበሩ ስራ ምክንያት በመደበኛ ስራው ላይ በማይገኝበት ሁኔታ ላይ ሲሆን የስራ አፈፃፀም ግምገማ በተመለከተ በሠራተኛ ማህበር መሪነት ከመመረጡ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘውን ነጥብ ይያዝለታል፡፡

7.7 ሠራተኛ ሲቀጥር ፣ ሲመድበና የስራ መደብ ለውጥ ሲያደርግ የሠራተኛው ፎቶ ግራፍ የተለጠፈበትና የሚሰራበትን ቦታና የሥራ መደብ የሚገልጽ ደረጃውን የጠበቀ የመታወቂያ ካርድ በነፃ ድርጅቱ ይሰጠዋል፡፡ መታወቂያው ካረጀ አሮጌውን አስረክቦ አዲስ ይለወጥለታል፡፡ ከጠፋበት ደግሞ ሠራተኛው መታወቂያው መጥፋቱን በማመልከቻ ለድርጅቱ በማሳወቅ ብር 25.00 ከፍሎ መታወቂያው ይለወጥለታል፡፡ ድርጅቱ ግን ለሚመለከተው የህግ አካል በደብዳቤ የሚያሳውቁ ሲሆን ሠራተኛው ይህን ተከታትሎ አስመስክሮ ደብዳቤ ማምጣት ይኖርበታል፡፡

7.8 የሠራተኛውን ጤንነት ፣ ደህንነትና የህሊና ክብር እንዲጠበቅ ተገቢውን ሁሉ ያደርጋል፡፡

7.9 የድርጅቱና የሠራተኛው ጥቅም የተሳሰረ መሆኑን በመረዳት የምርት መገልገያዎችና ማንኛውም የድርጅቱ ሀብታና ንብረት በጥንቃቄ እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡

7.10 አዲስ የሚቀጠሩ ሠራተኞችን አስፈላጊውን የቅጥር ፎርማሊቲ አሟልተው እንዲቀጠሩ ያደርጋል፡፡ በድርጅቱ ለስራ የሚቀጠሩ ሠራተኞች እድሜ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 89 ተራ ቁጥር 2 በተጠቀሰው መሰረት ከ15 ዓመት በላይ መሆን አለበት፡፡

7.11 ሠራተኛው የተቀጠረበትን የስራ መደብና ደረጃ ፣ የቅጥር ቀን ፣ የደመወዝ ልክ ፣ የትምህርት ማስረጃ ፣ የስራ ልምድ ፣ የስራ አፈፃፀም ግምገማ ፣ ዕድገት ያገኘባቸውን ማስረጃዎች ፣ ስልጠናዎች ፣ የወሰዳቸው ልዩ ልዩ ፍቃዶች ፣ የጤንነት ሁኔታዎችን እና ሌሎች ሠራተኛውን የሚመለከቱ ማስረጃዎችን በግልፅ በሚያሳይ የግል ማህደር በጥንቃቄ ያደራጃል ፣ ይይዛል፡፡

7.12 በዚህ ህብረት ስምምነት የተደነገጉ የዲሲፕሊን እርምጃ አወሳሰድ ፣ የቅሬታ አቀራረብ ስነ-ስርዓትና የመሳሰሉትን ጉዳዮች አፈፃፀም የመከታተል ግዴታ አለበት፡፡

7.13 ለእያንዳንዱ ሠራተኛ ለተመደበለት ስራ የስራ ዝርዝር መግለጫ በተጨማሪም ሠራተኛው የሚጠበቅበትን የስራ ውጤት የስራ አፈፃፀም መለኪያ ግብ አውቆ በስራ ላይ እንዲውል አዘጋጅቶ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡

7.14 ጤናማ የስራ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ፣ ከአደጋ ለመከላከል የሚያገለግሉና አደጋ በደረሰበት ጊዜ ለመጀመሪያ እርዳታ የሚያስፈልጉ የህክምና መሳሪያዎችን ፣ የመፀዳጃና የሰውነት መታጠቢያ ክፍሎችን ከፅዳት ሰራተኛ ጋር አሟልቶ ያቀርባል ፣ አፈጻጸሙንም በየጊዜው ይከታተላል፡፡

7.15 የሠራተኛ ማህበሩ እንዲጠናከር የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ ድርጅቱና ሠራተኛ ማህበሩ በሠራተኛ ማህበሩ ስር ለተቋቋሙት ብድርና ቁጠባ ህ/ስ/ማህበር ፣ ለሸማቾች ህ/ስ/ማህበርና ለሠራተኞች መረዳጃ ማህበር አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የሚቻለውን እገዛ ያደርጋል ፣ ያበረታታል፡፡

7.16 ከሠራተኛ ማህበሩ ጋር በመተባበር የህብረት ስምምነቱ አንቀፆች ትርጉምና አፈፃፀም ሠራተኞች እንዲረዱት ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ ለእያንዳንዱ ሠራተኛ አንድ ቅጅ የህብረት ስምምነት ኮፒ በፓኬት ሳይዝ አሳትሞ በነፃ ይሰጣል፡፡

7.17 ከመንግስት የበላይ አካል ሠራተኛውን በሚመለከት የሚተላለፉትን አዋጅና መመሪያዎች ለሠራተኛውና ለሠራተኛ ማህበሩ በወቅቱ ያሳውቃል፡፡

7.18 ሠራተኛው በየወሩ ለመክፈል የተስማማበትን ወርሃዊ የአባልነት መዋጮ ፣ ገንዘብና ብድር ቁጠባ ማህበር ፣ መረዳጃ ማህበር የሠራተኛ ማህበሩን መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በማድረግ በጠቅላላ ጉባኤ የሚወሰኑ ክፍያዎችን ድርጅቱ ከሠራተኛው ደመወዝ ቀንሶ በተቋሞቹ በተከፈተው የባንክ ሂሳብ ገቢ ያደርጋል፡፡ ሌሎች ክፍያዎችን በሚመለከት ለአፈፃፀም አመቺነቱን ድርጅቱ አረጋግጦ አከፈፋሉን የሚፈጽም ይሆናል፡፡

7.19 ድርጅቱ አጠቃላይ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታና ኦዲት የተደረገ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በዓመት አንድ ጊዜ ለሠራተኞች ያሳውቃል፡፡

7.20 የስራ ውል በሚቋረጥበት ወይም ሠራተኛው በሚጠይቅበት በማንኛውም ጊዜ ሠራተኛው ሲሰራ የነበረውን የስራ አይነት
፣ የአገልግሎት ዘመንና ሲከፈል የነበረውን ደመወዝ የሚያሳይ የምስክር ወረቀት በነፃ ይሰጣል፡፡

7.21 ይህን የህብረት ስምምነት ለማሻሻል ወይም በአዲስ የሥራ ሁኔታዎች ላይ ለመወያት ሠራተኛ ማህበሩ ሲጠይቅ በጋራ ፕሮግራም በማውጣት የመወያየት ግዴታ አለበት፡፡

7.22 የሠራተኛው ምርታማነት እንዲጨምር ፣ በወቅቱ በስራው ላይ እንዲገኝና ከስራ መልስ በወቅቱ ወደቤቱ እንዲገባ እንዲያስችል የሰርቪስ አገልግሎት መኪና ያመቻቻል ፣ ዝርዝር አፈፃፀሙን ድርጅቱ ለሠራተኛ ማህበር ያሳውቃል፡፡

7.23 የድርጅቱ ሠራተኞች ለህክምና ወደ አዲስ አበባ ሪፈር በሚባሉበት ጊዜ በድርጅቱ የህክምና አሰራር መሰረት የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ የረጅም ጊዜ ብድር ሊያመቻች ይችላል፡፡ የደርሶ መልስ ትራንስፖርት ወጪ በህዝብ ትራንስፖርት በሚቀርብ ደረሰኝ መሰረት ይሸፍናል፡፡

7.24 ድርጅቱ ለሴት ሠራተኞች የጡትና የማህፀና ጫፍ ቅድመ ካንሰር አስፈላጊውን ግንዛቤ እንዲያገኙ እና ምርመራ እንዲያደርጉ ከሚመለከተው የጤና ተቋም ጋር በመሆን ያበረታታል፡፡

7.25 ድርጅቱ ለሠራተኞች ከጡረታና ማህበራዊ ዋስትና አሰራር ጋር በተያያዘ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በወቅቱ ይልካል ፣ አፈጻጸሙንም በመከታተል የጡረታ ቁጥራቸውን ያሳውቃል፡፡ የጡረታ ጊዜያቸውም ሲደርስ የጡረታ አበል በጊዜው እንዲያገኙ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡

አንቀጽ ስምንት

ድርጅቱ ለሠራተኛ ማህበሩ የሚሰጠው ድጋፍና አገልግሎት

8.1 የሠራተኛ ማህበሩን ሥራ ለማከናወን በቂ የሆነ ቢሮ ከሙሉ መገለገያ ጋር ፣ የመስመር ስልክ ለሠራተኛ ማህበሩ ይሰጣል፡ ፡ የቀጥታ መስመር ሥልክ ክፍያን በተመለከተ ኪራዩን ጨምሮ ለተጠቀሙበት በየወሩ እስከ ብር 300.00 /ሦሰት መቶ ብር/ ድረስ ድርጅቱ ይሸፍናል፡፡

8.2 የሠራተኛ ማህበሩን ማስታወቂያና ትምህርታዊ ፅሁፍ የሚለጠፍበት ማስታወቂያ ሰሌዳ ያዘጋጃል፡፡

8.3 ሠራተኛ ማህበሩ ለልምድ ልውውጥና ሌሎች የስራ ጉዳዮች በአካባቢው በሚገኙ ተቋማት በሚንቀሳቀስበት ወቅት ቀደም ብሎ ፕሮግራም ማስያዝ እንዳለበት የተጠበቀ ሆኖ ድርጅቱ ትራንስፖርት አገልግሎት ሊያመቻች ይችላል፡፡ ከስራ ክልል ውጭ ከሆነ በድርጅቱ ባለቤት ወይም የበላይ ኃላፊ ውሳኔ የሚታይ ይሆናል፡፡

8.4 ሠራተኛ ማህበሩ ለማጠናከርና ለመደገፍ እንዲሁም ሠራተኞች ለሚያጋጥማቸው የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች እንዲውል በማሰብ ማህበሩ በየጊዜው በሚያቀርበው የድጋፍ ፕሮፖዛል ወይም እቅድ መሰረት በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙ ተረፈ ምርቶች እና የተለያዩ ያገለገሉ ወይም የተጋቡ ዕቃዎች በቅናሽ ለማህበሩ የሚሸጡበት ወይም በድጋፍ መልክ የሚሰጡበት ሁኔታ በድርጅቱ በኩል በየጊዜው እየታየ የሚወሰን ይሆናል፡፡

አንቀጽ ዘጠኝ

የሠራተኛ ማህበሩ መብት

9.1 በዚህ ህብረት ስምምነት ውስጥ ስለተመለከቱትም ሆነ ከስምምነቱ ውጭ ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ማንኛቸውም የሠራተኛው የሥራ ሁኔታዎች ሰራተኛውን ወክሎ ከአሰሪው ጋር የማነጋገር መብት አለው፡፡

9.2 ቅሬታ ወይም በደል ደረሰብን የሚሉ ሠራተኞችን ወክሎ ከአሰሪው ጋር የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 እና የህብረት ስምምነት በሚፈቅደው መሰረት ለመደራደር ወይም ሠራተኛን/ሠራተኞች/ ወክሎ ለመከራከር መብት አለው፡፡

9.3 በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/11 አንቀጽ 82 እና በህብረት ስምምነቱ በተወሰነው መሰረት የማህበሩ መሪዎች የሥራ ክርክር ለማቅረብ፣ የህብረት ስምምነት ለመደራደር ፣ በማህበር ስብስባ ለመገኘት ፣ በሴሚናሮችና በስልጠና ፈቃድ የመጠየቅ መብት አለው፡፡ ሆኖም በተጠቀሱት ስብሰባዎችና ስልጠናዎች ላይ የሚሳተፍ መሆኑን የሚያስረዳ የጥሪ ደብዳቤ ለድርጅቱ ማቅረብ አለበት፡፡

9.4 ሠራተኛ ማህበሩ ስለሠራተኛ ሁኔታ ከሌላ አካል ጋር ለሚቀርብበት ጥያቄ ማብራሪያ የመስጠትና የማነጋገር መብት አለው፡፡

9.5 ድርጅቱ በሚያዘጋጀው አዲስ የአሰራር ስርዓቶችና ማሻሻያዎች ፣ የስራ ዕቅድ እና ወቅታዊ የስራ አፈጻጸም ግምገማዎች ፣ የቅጥርና ዕድገት ኮሚቴ እንዲሁም የዲስፕሊን ኮሚቴ ላይ ሠራተኛ ማህበሩ የመሳተፍ መብት አለው፡፡

አንቀጽ አስር

የሠራተኛ ማህበሩ ግዴታዎች

10.1 የህብረት ስምምነቱ ፣ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011ን ትርጉምና አፈፃፀም ከድርጅቱ ጋር በመተባበር ሠራተኛው እንዲረዳ ያደርጋል፡፡

10.2 ይህንን የህብረት ስምምነት ለማሻሻል ወይም በአዲሱ የስራ ሁኔታዎች/የአሰራር ስርአቶችና ማሻሻያዎች/ ላይ ድርጅቱ ለውይይት ሲጠራ ቀርቦ ይወያያል ፣ አማራጭ ሀሳቦችንም ይሰጣል፡፡

10.3 የህብረት ስምምነቱን ህጎችና የመንግስት መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ አሰሪው የሚያወጣቸውን መመሪያዎችና የሥራ ዕቀዶችን ያስፈጽማል፡፡

10.4 በድርጅቱ የስራ አካባቢዎች ሰራተኛው የስራና ስነ-ምግባር ዲሲፕሊን እንዲያከብርና የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ ያደርጋል፡፡

10.5 ሰራተኛው የስራ ሰዓት አክብሮ መላው ጉልበቱንና ችሎታውን በሥራ ላይ አውሎ ምርቱን በጥራትና በብዛት እንዲያመርትና የድርጅቱን ዕቅድ እንዲሳካ ያስተባብራል፡፡

10.6 የሥራና የአደጋ መከላከያ አልባሳትን ሰራተኛው እንዲጠቀም ሰራተኛ ማህበሩ ከድርጅቱ ጋር በመሆን ያስፈጽማል፡፡

አንቀጽ አስራ አንድ

የሠራተኛ መብቶች

11.1 በመንግስት ህጎች ፣ መመሪያዎች ፣ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ 1156/2011 እና በዚህ ህብረት ስምምነት ውስጥ ለተጠቀሱት የሥራ ሁኔታዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት አለው፡፡

11.2 በህግ ወይም በህብረት ስምምነት፣ በሠራተኛ ማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት በሥራ ደንብ በተወሰነው ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዛ መሰረት ካልሆነ ወይም ሠራተኛው በፅሁፍ ካልተስማማ በስተቀር ድርጅቱ ከሠራተኛ ደመወዝ ሊቀነስ ወይም በእዳ ሊይዝ ወይም ሊያቻችል አይችልም፡፡

11.3 በስራ ውሉ ላይ በተጠቀሰው መሰረት የሚከፈለውን ደመወዝና ሌላም ህጋዊ ክፍያ ወይም ጥቅም በወቅቱ የማግኘት መብት አለው፡፡

11.4 ማንኛውም የድርጅቱ ሠራተኛ በሠራተኛ ማህበሩ አማካኝነት ወይም በግሉ ቅሬታውን ወይም አቤቱታውን ለግልግል ዳኞች ወይም ሥራ ክርክር ችሎት ለማቅረብ ህጋዊ መብቱን ለማስከበር ይችላል፡፡

11.5 ማንኛውም ሰራተኛ በግል ማህደሩ ላይ ጥርጣሬ ሲኖረው በሰው ሃይል ልማትና አስተዳደር መምሪያ በኩል አስቀርቦ የማየት መብት አለው፡፡

11.6 የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 እንደተጠበቀ ሆኖ በሰራተኛው ጥፋት ወይም ቸልተኝነት ሳይሆን በመሳሪያ ብልሽት ወይም በጥሬ ዕቃ እጥረት ሠራተኛው ሳይሰራ ቢውል የዕለቱን መደበኛ ደመወዝ ያገኛል፡፡

11.7 ሴት ሠራተኞች ሲወጡና ሲገቡ የሚፈትሹት በሴት ሠራተኞች ነው፡፡

11.8 ሠራተኛው በማንኛውም ስብሰባ ወይም በማንኛውም ህጋዊ መንገድ ሃሳቡንና ቅሬታውን መግለፅና ማቅረብ ይችላል፡፡

11.9 ማንኛውም የድርጅቱ ሠራተኛ የሆነ ወይም የነበረ አስፈላጊውን የበር መግቢያና መውጫ ፎርማሊቲ አሟልቶ ለአስተዳደራዊ ስራዎች እና የመብት ጥያቄ ለማቅረብ ወደሚመለከተው ክፍል መግባት ይችላል፡፡

11.10 ማንኛውም የኤች አይ.ቪ. ቫይረስ በደሙ የተገኘበት ሰራተኛ ስለተገኘበት ብቻ ከመደበኛው ሥራው ላይ ምንም አይነት አድሎና መገለል አይደረግም፡፡

11.11 የእድሜ ጣራው ለጡረታ የደረሰ ሠራተኛ ጡረታ ከሚወጣበት ጊዜ 6 ወር ቀድሞ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ይሰጠዋል፡፡ የጡረታ ጊዜው ደርሶ የጡረታ ደብተሩ ያልደረሰውና ቀሪ ሥራ የቀረው ከሆነ እስከስድስት ወራት ለሚደርስ ጊዜ ድርጅቱ በኮንትራት ቀጥሮ እያሰራው እንዲቆይ ይደረጋል፡፡

አንቀጽ አስራ ሁለት

የሠራተኛ ግዴታዎች

12.1 በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ፣ በዚህ ህብረት ስምምነትና ለሥራ ማሻሻያ ከመንግስትና ከድርጅቱ የሚተላለፉትን ደንቦች የማክበር ፣

12.2 ማንኛውም ሠራተኛ በቅልጥፍናና በተሟላ ትጋት ሥራውን የማከናወን ፣

12.3 ማንኛውም የድርጅቱ ሰራተኛ አስቀድሞ ፈቃድ ካልተሰጠው በስተቀር በመደበኛ ሥራው ላይ የድርጅቱን የስራ ሰዓት አክብሮ በስራ ላይ የመገኘት ፣

12.4 በድርጅቱ ላይ ወይም በስራ ባልደረቦች የሚያጋጥም ጉዳት ወይም አደጋ ላይ በተፈለገው ሁኔታ ሁሉ እርዳታ የመስጠት፣

12.5 ለሥራው አስፈላጊ ሆነው የተሰጡትን መሳሪያዎችና ሌሎች ንብረቶችን በጥንቃቄ መያዝና ለስራ ብቻ የመጠቀም ፣ የስራ ሰዓት ሲፈጸም በሚገባ የማስቀመጥ ፣

12.6 የሥራ አፈፃፀም ምዘና ሥርዓት ፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የምርት ስራ አመራር ሥርዓት ፣ የካይዘን እና ሌሎች አዳዲስ የለውጥ ስራ አመራር አሰራሮች የመቀበል እና በአግባቡ የመተግበር ፣

12.7 በድርጅቱ ወይም በድርጅቱ መሳሪያዎች ላይ የሠራተኛውን ደህንነትና ጤንነት የሚጎዳ ሁኔታ ሲያገኘ የሚደርሰውን ማንኛውንም አደጋ ወዲያውኑ ለአሰሪው የማሳወቅ ፣

12.8 በሥራ ላይ መተባበርና ለድርጅቱ ጥቅም የለውጥ እንቅስቃሴ አሰራር ላይ አንድነት የማሳየት ፣

12.9 ማንኛውም ሰራተኛ ከሚመለከተው ኃላፊ የጽሁፍ ፈቃድ ሳይሰጠው የድርጅቱን ንብረት የሆነውን ማንኛውንም አይነት ምርት ወይም ጥሬ ዕቃ፣ መገልገያ ዕቃ ከድርጅቱ ቅጥር ግቢ በማውጣት፣ ለራሱ ሊገለገልበት ወይም ለሌላ ግለሰብ አሳላፎ ለመስጠትና ከጥቅም ውጭ ማድረግ የለበትም፡፡

12.10 በአሰሪውና በሰራተኛው ማህበር ወይም በአሰሪውና በሰራተኞች መካከል ወይም በሰራተኞች መካካል አለመግባባት የመፍጠር፣ የሀሰት ወሬ አሉባልታ መንዛትና ጠብ ማንሳት ወይም እንዲነሳ መገፋፋት ወይም እራሱንም ሆነ የሥራ ጓደኞቹን አደጋ ላይ የሚጥል ወይም የድርጅቱን ጥቅም የሚነካ ሁኔታ ሲያጋጥመው ወዲያውኑ ለአሰሪው የማሳወቅ ፣

12.11 ማንኛውም ሰራተኛ በድርጅቱ የሥራ ሰዓት ወደድርጅቱ መግባት ሲፈልግ ወይም የሚያስገባ ጉዳይ ሲያጋጥመው ለጥበቃ ክፍል መታወቂያውን ማሳየት ይኖርበታል፡፡

12.12 ማንኛውም ሠራተኛ በስራ ሰዓትና ቦታ መተኛት የለበትም፡፡

12.13 ሠራተኛው አዕምሮውን በሚያደነዝዝ አነቃቂ ዕፅ እና አልኮል መጠጥ ኃይል ተመርዞ በስራ ላይ መገኘት የለበትም፡፡

12.14 በድርጅቱ ከተቀጠረ በኋላ ከድርጅቱ ሳይለቅ በሌላ መ/ቤት ቋሚ ሠራተኛ ሆኖ መቀጠር አይችልም፡፡

12.15 በሥራ ሰዓትም ሆነ ሥራ ሰዓት መካከል በሚሰጥ የዕረፍት ጊዜ በድርጅቱ ንብረት ለውጭ አካል ወይም ለራሱ የግል ሥራ መስራት አይችልም፡፡

12.16 ድርጅቱና ማህበሩ ካልፈቀዱ በስተቀር በሥራ ቦታ ወይም በማንኛውም ጊዜ በድርጅቱ ውስጥ ልዩ ልዩ እትሞች ፣ ፅሁፎችና የማስፈረሚያ ሊስት የመሳሰሉትን የመፃፍ ፣ የማስፈረም ፣ የመፈረም ፣ የመለጠፍ ወይም ማዞር የተከለከለ ነው፡፡ ነገር ግን ሠራተኛ ማህበሩ የምክር ቤት አባላቱን ስብሰባ መጥረት በፈለገበት ጊዜ በስብሰባው ላይ እንዲገኙ የስብሰባ ጥሪ ቅጽ አዙሮ ሊያስፈርም ይችላል፡፡

12.17 ድርጅቱ አውቆ የፈቀደው ወይም በዚህ ህብረት ሥምምነት ከተደነገገው ውጭ በድርጅቱ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ ስብሰባ ማድረግ አይፈቀደም፡፡

12.18 ከድርጅቱ ስራ ጋር የተያያዘ ሁኔታ ጉቦ ወይም ጉርሻ ፣ መደለያ ፣ ኮሚሽንና የመሳሰሉትን መደራደሪያዎች መቀበል የለበትም፡፡

12.19 ወደድርጅቱ ድምፅ ያለውንም ሆነ ድምፅ የሌለውን ወይም ተቀጣጣይ መሳሪያ ፣ አልኮል እና አደንዛዥ ዕጾችን ይዞ መግባት አይፈቀድም፡፡

12.20 ሠራተኛው የሚሰጠውን የሥራ ልብስና የአደጋ መከላከያ መጠቀም ግዴታ አለበት፡፡ የሌላ ድርጅት አርማ ያለው እና የተቀደደና ደረጃውን ያልጠበቀ የሥራ ልብስ መልበስ የተከለከተለ ነው፡፡

12.21 ለሥራው መቃናት ሲባል አንድ ሰራተኛ ደረጃውና ጥቅሙን ተጠበቆ ከሚሰራበት ቦታ ወይም ፈረቃ እንዲዛወር ሲጠየቅ በቅድሚያ በፈቃደኝነት መፈጸምና በተመደበበት ቦታ ተገኝቶ ስራውን መስራት አለበት፡፡ ቅሬታ ካለው በተዛወረበት ወይም በተመደበበት የሥራ ቦታ እየሰራ መጠይቅ ይችላል፡፡

12.22 ማንኛውም ሠራተኛ በማንኛውም አይነት ፈቃድ ወይም በማንኛውም ህጋዊ በሆነ ምክንያት ከመደበኛ ስራው ላይ የማይኖር ከሆነ ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር በቅድሚያ ለአሰሪው አሳውቆ እንደስራው ፀባይ በእጁ የሚገኘውን እቃና በጅምር ላይ ያለውን ሥራ ሁሉ ለቅርብ ኃላፊው የማስረከብ አለበት፡፡

12.23 ማንኛውም ሠራተኛ የድርጅቱን የአሰራር ሚስጥር ወይም ሌሎች መረጃዎችን አሳልፎ ለግል ጥቅም ማግኛ ወይም የድርጅቱን ጥቅም የሚነካ ማንኛውንም ተግባር መፈፀም የለበትም፡፡

12.24 ማንኛውም ሠራተኛ የድርጅቱ ሆነ የማህበሩ ንብረት ሲባክን ሲያይ ወይም ሲያውቅ ለሚመለከተው ክፍል ወዲያውኑ የማሳወቅ አለበት፡፡

12.25 ማንኛውም ሠራተኛ ወደ ድርጅቱ ቅጥር ግቢ ሲገባና ሲወጣ ተሽከርካሪ ካለ ለፍተሻ የመተባበርና በተፈቀደ ቦታ ብቻ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡

12.26 ማንኛውም የጥበቃ ሠራተኛ ቀንም ሆነ ሌሊት በተመደበበት ቦታና ሰዓት በንቃት መገኘት አለበት፡፡

12.27 ማንኛውም ሠራተኛ የማይገባውን ጥቅም በስህተት ከተቀበለ የመመለስና የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡

አንቀጽ አስራ ሶስት

የስራ ውል አመሰራረት ፣ የሠራተኛ ቅጥር፣ ምደባ፣ ሥልጠና፣ ግምገማ፣ ዕድገትና ዝውውር

13.1 ጠቅላላ

1. ድርጅቱ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/11 ህግን ተከትሎ በሚወጣ የድርጅቱን መመሪያና በዚህ ህብረት ስምምነት መሰረት ሰራተኛን መቅጠር፣ ማሳደግ፣ ለሥራ ብቃት ያለው ነው ብሎ ያመነበትን ሰራተኛ አወዳድሮ ለመመደብ ወይም አዛውሮ ለማሰራት ይችላል፡፡

2. በአዋጅና ሌሎች መመሪያዎች የተሰጡትን ግዴታዎችና ህግን ተከትሎ ድርጅቱ የሚያወጣቸውን መመዘኛ/መዋቅር/ የሚያሟላ ሆኖ ከተገኘ በሀይማኖት፣ በፆታ፣ በብሄር፣ በፖለቲካ ልዩነት ሳይደረግበት በድርጅቱ በሚፈጠሩ ክፍት የስራ ቦታዎች ይወዳደራል፡፡

3. ለድርጅቱ መስፋፋት ወይም ለምርት ዕድገት የተለየ ሙያን የሚጠይቅ ተጨማሪ የሰው ሃይል አስፈላጊ ሲሆን አዲስ የሥራ ቦታ መፈጠሩን ወይም የተለያዩ ተመሳሳይነት ያላቸው እና ከኬሚካል ጋር ተያይዞ ችግር ሊያስከትሉ በማይቻሉ የስራ መደቦች ላይ ሰራተኛ መመደብ አስፈላጊ መሆኑን ህግን ወይም ህብረት ስምምነትን ተከትሎ የሚወሰነው አሰሪው ነው፡፡

4. በተለቀቀም ሆነ አዲስ በተፈጠረ የሥራ መደብ የሚፈለገውን የትምህርት ደረጃና የሙያ አይነት፣ ደመወዝ፣ እንዲሁም ተፈላጊውን የሥራ ልምድ የሚወሰነው ድርጅቱ ነው፡፡

5. ለሥራው ብቁ ሆኖ ለታመነበት ሰራተኛ የቅጥር ደብዳቤው ከመሰጠቱ በፊት ተቀጣሪው ሰራተኛ ድርጅቱ የሚጠይቃቸውን መረጃዎች በቅድሚያ የማሟላት ግዴታ አለበት፡፡

6. ድርጅቱ የመንግስት ደንብ እንደተጠበቀ ሆኖ አዲስ ሰራተኛ ሲቀጥር ወይም ከውስጥ ሰራተኛ በንብረት ወይም በገንዘብ ነክ በሆነ ስራ ላይ በዝውውር /ዕድገት/ ሲመደብ ዋስ እንዲያቀርብ ያደርጋል፡፡

7. አዲስ ወይም ነባር ሰራተኛ ፋብሪካው በሚያወጣው ዕቅድ መሰረት ማንኛውንም የሙያ ደህንነት ጤንንት ሥልጠና ድርጅቱ በነፃ ይሰጣል፡፡

8. የሰራተኛ አቀጣጠር ሥርዓት ሠራተኛው ሊቀጠር የሚችለው ከዚህ በታች በተመከተቱት ምክንያቶች ነው፡፡

9. ለድርጅቱ መስፋፈት ወይም የምርት ዕድገት የተለዬ ሙያ የሚጠይቅ ተጨማሪ የሰው ሃይል አስፈላጊ መሆኑን ድርጅቱ ሲወሰን፡፡

10. አዲስ የሥራ መደብ ተፈጥሮ ወይም ነባር የሥራ ቦታ ተለቆ ወይም ተቀይሮ/ተዳልቦ/ በድርጅቱ የሰው ኃይል አደረጃጀት መሰረት ለቦታው የወጣውን መስፈርት የሚያሟላ ሰራተኛ ከድርጅቱ ሠራተኞች ውስጥ ሲታጣ ፣

11. ለተወሰነ ስራ ወይም ለተወሰነ ጊዜ መመሪያን በመከተል ሰራተኛ የሚቀጠርበት ሁኔታ ሲያጋጥም ፣

12. በህጉ መሰረት የውጭ ሀገር ዜጋ መቅጠር ሲያስፈልግ ፣

13.2 የስራ ውል አመሰራረት

1. ማንኛውም የስራ ውል የሥራውን አይነት፣ ቦታ ፣ ለስራው የሚፈለውን ደመወዝ መጠን፣ የስሌት ዘዴን፣ የአከፋፈሉን ሁኔታና ጊዜ፣ የሙከራ ጊዜና የስራ አፈፃፀም መለኪያ ግብና ውሉ ጸንቶ የሚቆይበትን ጊዜ መያዝ ይኖርበታል፡፡

2. የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ 1156/2011 ፣ መንግስት በየጊዜው የሚያወጣቸው መመሪያዎችና ደንቦች እንዲሁም ህብረት ስምምነት ከሥራ ውል እንደአንዱ የሚቆጠሩ ይሆናሉ፡፡

3. ለተወሰነ ጊዜ ወይም ለተወሰነ ሥራ ሰራተኛ የሚቀጠረው በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/11 አንቀጽ 10 መሰረት ነው፡፡

13.3 የሙከራ ጊዜ ቅጥር

1. የማንኛውም የቋሚ ስራ ተቀጣሪ ሠራተኛ የሙከራ ጊዜ ከ60 የስራ ቀናት መብለጥ የለበትም ይህም ለሠራተኛው በቅጥር ደብዳቤው ወይም በስራ ውሉ ላይ ይገለፃል፡፡

2. በሙከራ ጊዜ ላይ ያለ ሠራተኛ ለስራው ብቁ ካልሆነ ድርጅቱ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ፣ የሥራ ስንብት ክፍያ፣ የአገልግሎት ክፍያና ካሳ ሳይከፈል ሊያሰናበት ይችላል፡፡

3. ሠራተኛው በሙከራ ጊዜ መጨረሻ በአሰሪው አስተያየት ለሥራው አጥጋቢ ወይም ብቁ መሆኑ ከተረጋገጠ ለሙከራ ጊዜ ከተቀጠረበት ጊዜ ጀምሮ በቋሚነት የተቀጠረ መሆኑ በጽሁፍ ይገለጽለታል፡፡ ሠራተኛው የሙከራ ጊዜው ካለቀ በኋላ ስራውን ከቀጠለ በውሉ መሰረት ለታቀደው ጊዜ ወይም ሥራ እንደተቀጠረ ይቆጠራል፡፡

4. በሙከራ ላይ ያለ ሠራተኛ ያለ ማስጠንቀቂያ ሥራውን ሊለቅ ይችላል፡፡

5. በሙከራ ላይ ያለ ሠራተኛ እንደሥራው ፀባይ የአደጋ መከላከያ ይሰጠዋል፡፡ ሆኖም የሙከራ ጊዜውን ከመጨረሱ በፊት ለቋሚ ሰራተኛ የሚሰጠውን ጥቅማ ጥቅም ሊያገኝ አይችልም፡፡

6. ሠራተኛው ቀድሞ ይሠራው በነበረ ሥራ እንደገና በአሠሪው ቢቀጠር ለሙከራ ጊዜ ሊቀጠር አይችልም፡፡

13.4 የሠው ኃብት ልማትና ስልጠና

1. ሠራተኛው እውቀቱን አሻሽሎ የተመደበበትን ሥራ በብቃት እንዲወጣ ከቅጥር በፊት ስራውን ከሠራተኛ ጋር ለማስተዋወቅ እንዲሁም የሙከራ ጊዜያቸውን የጨረሱ ሠራተኞች የተመደቡትን ስራ ብቃት እንዲወጡ ወይም በእድገትና በዝውውር ምክንያት ለተጨማሪ ሃላፊነትና የሥራ ብቃት ዝግጁ እንዲሆኑ ድርጅቱ ሲያምንበት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር አስፈላጊውን ሥልጠና እንዲያገኙ ይመቻቻል፡፡

2. በማንኛውም ህጋዊ በሆነ የስልጠና ተቋም ለስልጠና ተልኮ ስልጠናውን ያጠናቀቀ ሠራተኛ በሰለጠነበት መስክ ያገኘውን ሠርትፍኬት ለሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር ሲያቀርብ ከዋናው ጋር ተገናዝቦ ከግል ማህደሩ ጋር ይያያዝለታል፡፡

3. በማንኛውም ሁኔታ በስልጠና ላይ የቆየ ሰራተኛ የሥልጠና ሪፖርት እንዲሁም በስልጠና ወቅት ያገኛቸውን የጽሁፍ እና ኤሌክትሮኒክ መረጃዎች ወይም የሥልጠና ማኑዋል ኮፒዎች ለሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር መምሪያ መስጠትና የሰለጠነውን ሥልጠና ለሌሎች እንዲያስተምር ሲጠየቅ ተዘጋጅቶ ሥልጠና ይሰጣል፡፡

4. ድርጅቱ ሠራተኞች ዕውቀታቸውን በትምህርት እንዲያሻሽሉ ያነቃቃል፡፡

5. ሠራተኛው ትምህርት ለመማር የሰራተኛው የትምህርት ጊዜ ከመደበኛው የድርጅቱ የስራ ሰዓት ጋር በማይጋጭ መልኩ የሚማሩትን ሰራተኞች ያበረታታል፡፡

6. የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን መስፈርቱ በድርጅቱ በሚዘጋጅት የትምህርትና ስልጠና መመሪያ መሰረት የሚፈጸም ይሆናል፡፡

7. በድርጅቱ የትምህርትና ስልጠና መመሪያ መሰረት ማንኛውም ሰልጣኝ ከሰለጠነ በኋላ ድርጅቱን እንዲያገለግል ግዴታ ያስገባዋል፡፡

13.5 የስራ አፈፃፀም ምዘና

1. የስራ አፈፃፀም ምዘና ሰራተኛው ያለው አዕምሮዊና አካላዊ ችሎታውን በመጠቀም በድርጅቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ ውስጥ የተቀመጡትን አላማና ግቦች ለማሳካት የተሰጡትን ተግባራት ማከናወኑን በተቀናጃ ሁኔታ ለመመዘን የሚረዳ የምዘና ስርዓት ነው፡፡

2. የስራ አፈፃፀም ምዘና በድርጅቱ መመሪያ መሰረት ይሞላል፡፡

3. የስራ አፈፃፀም ምዘና በሠራተኛው የቅርብ የስራ ኃላፊ ተሞልቶ በየደረጃው ባሉት የስራ ሃላፊዎች ከፀደቀ በኋላ አንዱ ቅጂ ለሰው ኃብት ልማትና አስተደደር መምሪያ ይላካል፡፡ ሁለተኛው ቅጂ በሚሰራበት መምሪያ ወይም ክፍል ፋይል ይደረጋል፡፡

4. የስራ አፈፃፀም ምዘና ሪፖርት በአመት ሁለት ጊዜ ሆኖ የመጀመሪያው ከሐምሌ 1 - ታህሳስ 30 ድረስ እና ሁለተኛው ከጥር 1- ሰኔ 30 ይሞላል፡፡ ነገር ግን የምዘና ሪፖርት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለሰ/ኃ/ል/አ/መምሪያ መቅረብ አለበት፡፡

5. የስራ አፈፃፀም ምዘና ሪፖርት የሚሞላ ሃላፊ በተጨባጭ ሁኔታዎች ለመመዘንና እያንዳንዱ ተመዛኝ ደካማና ጠንካራ ጎኖች በየጊዜው በመመዝገብ የመያዝና የስራ አፈፃፀም ምዘና ሪፖርቱን በጥንቃቄና በትክክል የመሙላት ሃላፊነት አለበት፡፡ ገምጋሚው ሲጠየቅ ማረጋጋጫ የማቅረብና የማስረዳት ኃላፊነት አለበት፡፡

6. አንድ ሰራተኛ ያገኘውን የምዘና ውጤት እንዲያውቅና እንዲፈርምበት ይደረጋል፡፡ ሰራተኛው በወቅቱ ቅሬታ ካለው ቅሬታውን በፅሁፍ ማቅረብ ይችላል፡፡ የበላይ ሃላፊ ባቀረበው ቅሬታ ላይ አስተያየቱን ሰጥቶበትና ለሰራተኛው ገልፆለት ተገምጋሚው በተሰጠው መልስ የማይረካ ከሆነ የስራ አፈፃፀሙን ምዘና በክፍሉ መምሪያ ስራ አስኪያጅ ወይም በአገልግሎት ስራ አስኪያጅ ቀርቦ ያላመነ ከሆነ ለሰ/ኃ/ል/አ/መምሪያ ስራ አስኪየጅ ያቀርባል፡፡ አሁንም በመልሱ ካልረካ ቀጥሎ ለሚገኘው የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ማቅረብ ይችላል፡፡

13.6 የደረጃ ዕድገት

1. የደረጃ ዕድገት በተለያየ ምክንያት ክፍት በሆኑ የስራ መደቦች ላይ የውስጥ ሠራተኞችን ከዝቅተኛ የስራ መደብ ወደከፍተኛ የስራ መደብ አወዳድሮ የመመደብ አሰራር ነው፡፡

2. የደረጃ ዕድገት የሚሰጠው ነባር ሰራተኛ በተለያዩ ምክንያቶች የስራ መደቡን ሲለቅና የድርጅቱ ስራ በመስፋፋቱ ምክንያት የሚፈጠሩትን ክፍት የስራ መደቦች ለስራ መደቡ የወጣውን መመዘኛ በሚያሟሉ ሰራተኞች እንዲሟላ ድርጀቱ ሲፈቅድ ነው፡፡

3. የስራ መደቡ የሚጠይቀውን የትምህርት ደረጃና መመዘኛ የሚያሟሉ ሰራተኞች ተወዳድረው የስራ መደቦችን እንዲሸፍኑ ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡ ከውጭ ሰራተኛ ከመቀጠሩ በፊት ይህንን የሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር መምሪያ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ሆኖም ገንዘብ ያዥ ፣ ሽያጭ ሠራተኛ ፣ ኦዲት ፣ ጥበቃ ፣ ንብረት ሠራተኛ እንዲሁም ከመረጃና ከድርጅቱ ገፅታ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የስራ መደቦች በመስፈርቶች ተወዳድረው ሲቀጠሩ ወይም ሲመድብ በቂ ዋስትና እንዲያቀርብ ይደረጋል፡፡

4. በደረጃ ዕድገት እንዲሞላ የተፈለገው ክፍት የስራ መደብ በሰው ኃብት አደረጃጀት ወይም ማኒንግ ቴብል መሰረት ለቦታው የሚያስፈልገውን የትምህርት ደረጃ ፣ የስራ ልምድና ሌሎች ተፈላጊ ማስረጃዎች የማረጋገጥ ኃላፊነት የድርጅቱ ነው፡፡ የእድገት ኮሚቴው ፈተና ከመሰጠቱ በፊት በመስፈርቱ የተሰጡትን ውጤቶች ትክክለኛነቱን ያረጋግጣል፡፡

5. በደረጃ ዕድገት እንዲሞላ የተፈቀደ ክፍት የስራ መደብ የድርጅቱ መዋቅር እንደተጠበቀ ሆኖ የሚያስፈልገውን የስራ ደረጃ የስራ ልምድና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን ያሟሉ ሰራተኞችን እንዲወዳደሩ አሰሪው ማስታወቂያ እንዲወጣ ያደርጋል፡፡ የድርጅቱ ማኒንግ ቴብል እንደተጠበቀ ሆኖ በጥናት ላይ የተቀመጠውን መስፈርት የሚያሟላ ሰራተኛ ሲጠፋ ድርጅቱ መንግስት እንደየሁኔታው በሚያወጣው የትምህርት ፖሊሲ ትንተና መሰረት የሚፈጸም ይሆናል፡፡

6. ድርጅቱ ለደረጃ ዕድገት የቀረበ ተወዳዳሪ ወይም የቀረቡ ተወዳዳሪዎችን የትምህርት መረጃ ፣ የስራ አፈፃፀም ምዘና ፣ በሥራው ያላቸውን ፍላጎትና ዝንባሌ ፣ ችሎታቸውን ለመገምገምና ለሚወዳደርበት ቦታ ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የፅሁፍ፣ በቃልና የተግባር ፈተና እንደሥራው ፀባይ በአንድ ወይም በሁለት ወይም በሶስትም ፈተናዎች ሊወሰን ይችላል፡፡

7. እያንዳንዱ እጩ ተወዳዳሪ ለፈተና ለመቅረብ የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ተገምግሞ ውጤቱ አጥጋቢና ከዚያ በላይ ሆኖ ለመጨረሻ ውድድር ለማቅረብ ግን አገልግሎት ሰጪ ከሆነ በጽሁፍና በቃል ፈተና ፣ በቴክኒካል ወይም ሙያዊ የስራ መደቦች ላይ ከሆነ በፅሁፍና በተግባር ፈተና ግማሽና ከግማሽ በላይ ውጤት ማግኘት ይኖርበታል፡፡

8. የሠራተኛ ቅጥርና ደረጃ ዕድገት በዚህ ህብረት ስምምነት ውስጥ በተዋቀረው የቅጥርና ደረጃ ዕድገት ኮሚቴ መሰረት ይፈፀማል፡፡

9. ሠራተኛ ማህበሩ በሠራተኛ ቅጥርና ደረጃ ዕድገት ኮሚቴ በአባልነት ይሳተፋል፡፡

10. የቅጥርና ደረጃ ዕድገት ኮሚቴው የውሳኔ ሀሳብ ተፈፃሚነት የሚኖረው በዋና ሥራ እስኪያጅ ወይም እርሱ በሚወክለው ኃላፊ ሲፀድቅ ብቻ ነው፡፡

11. የማኔጅመንት አካል ወይም የስራ ኃላፊ ለሆኑ የሥራ መደቦች ላይ ድርጅቱ ብቃት አለው ብሎ ያመነበትን መመደብ ይችላል፡፡

12. ድርጅቱ የሠራተኛ ቅጥርና ዕድገት ሲወጣ የሠራተኛ ማህበሩ በግልባጭ እንዲያውቀው ይደረጋል፡፡

13. አንቀጽ 7.2 እንደተጠበቀ ሆኖ ለደረጃ ዕድገት ቦታ ውድድር በሚደረግበት ጊዜ ሁለት ወይም ከሁለት በለይ ተወዳዳሪዎች ውጤታቸው እኩል ከሆነ አግባብ ባለው የሥራ ልምድና አገልግሎት ብልጫ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ የሴቶች 3 ነጥብ እንደተጠበቀ ሆኖ ለዕድገት ቦታ ውድድር በሚደረግበት ጊዜ የሁለት ወይም ከሁለት በላይ ተወዳዳሪዎች እኩል ከሆነ አግባብ ባለው የስራ ልምድና አገልግሎት ብልጫ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡

14. አንድሠራተኛ በዕድገት በተመደበበት የሥራ መደብ ላይ ቢያንስ 6 (ስድስት) ወራት ሳያገልግል በሌላ አዲስ ዕድገት ሊወዳደር አይችልም፡፡ አዲስ ተቀጣሪም 6 (ስድስት) ወራት ሳይገለግል በዕድገት አይመደብም፡፡ ነገር ግን ተወዳዳሪ ሳይቀርብ ወይም ተወዳዳሪዎቹ በሙሉ በተለያዩ ምክንያት ከውድድሩ ውጪ ከሆኑ ወይም ከወደቁ የተጠቀሰው ጊዜ ሳይጠበቅ ከክፍላቸው ድጋፍ የቀረበላቸው ሠራተኞች የሥራ አፈፃፀም ምዘና ውጤታቸው 90% እና ከዚያ በላይ ከሆኑ ለውድድር እንዲቀርቡ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህም ሆኖ ክፍት የስራ መደቡን ለማሟላት ካልተቻለ እና አማራጭ ከታጣ ድርጅቱ አስፈላጊውን ሊፈፅም ይችላል፡፡

15. ድርጅቱ ለውድድር የወጣው የቅጥርም ሆነ የዕድገት ማስታወቂያ ቅጥር ወይም ዕድገት ከመፈጸሙ በፊት ስህተት መሆኑ ሲደርስበት በማናቸውም ወቅት ማስታወቂያውን የመሰረዝ መብት አለው፡፡

16. ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር በማስታወቂያ መሰረት የተመዘገቡ ተወዳዳሪዎች ከ15 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለውድደር ወይም ለፈተና መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

17. ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር መመዘኛውን አሟልተው የተፈተኑ ተወዳዳሪዎች የፈተና ውጤት ከ15 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡

13.7 የቅጥርና ደረጃ ዕድገት ኮሚቴ አወቃቃር

1. የዕድገት ኮሚቴ የሚከተለው አባላት ይኖሩታል፡፡

1. የሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር መምሪያ ሥራ አስኪያጅ/ተወካይ/ --------------- ሰብሳቢ
2. ዕድገት፣ ቅጥር የሚደረግበት መምሪያ ሥ/አስኪያጅ/ተወካይ/ ---------------------- አባል
3. በድርጅቱ የሚወከል ኃላፊ/ተወካይ/ ---------------------------------------------------- አባል
4. የመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ተወካይ ------------------------------------------------- አባል
5. የሠራተኛ አስተዳደር ና ጠቅላላ አገ/ ዋና ክፍል ኃላፊ/ተወካይ/ -------------------- አባልና ፀሃፊ

2. የደረጃ እድገት መወዳደሪያ ነጥቦች አሰጣጥ የሚከተሉትን ይመስላል፡፡

1. የስራ አፈጻጸም ምዘና ---------------------------------------- 40%
2. የትምህርት ዝግጅት ------------------------------------------ 15%
3. ለቀጥታ አግባብ ያለው ሥራ ልምድ ----------------------- 15%
4. በድርጅቱ ውስጥ ላለው አገልግሎት ----------------------- 15%
5. ለማህደር ጥራት ---------------------------------------------- 10%
6. ከስራው ጋር ተዛማጅነት ያለው ስልጠና ------------------ 5%
ድምር -------------------------------------------------------------- 100%

3. ለስራ ልምድ የተያዘው 15% በቀጥታ አግባብነት ላለው የሥራ ልምድና በተዘዋዋሪ አግባብነት ላለው የሥራ ልምድ ብቻ ሲሆን፣ ለአገልግሎት ዘመን 15% በድርጅቱ ውስጥ ላለው አገልግሎት ያሉትን የስራ ዘመናት ብቻ ነው፡፡

ሀ. ነጥብ አሰጣጥ

የፅሁፉ ወይም የተግባር ፈተና

1. የፅሁፍ ፣ የቃል ወይም የተግባር ፈተና እንደአስፈላጊነቱ በድርጅቱ ውስጥ ወይም ከድርጅቱ ውጭ ሊሰጥ ይችላል፡፡
2. ክፍት የስራ መደቡ ቴክኒካል ወይም ሙያ ነክ ከሆነ ለተግባር ፈተና 25% ለፅሁፍ 10% ይሆናል፡፡
3. ክፍት የሥራ መደቡ የአገልግሎት ወይም ድጋፍ ሰጪ ከሆነ ለፅሁፍ ፈተና 25% ሲሰጥ ለቃል ፈተና 10%

ይሆናል፡፡ ለ. ስለ ፈተና አሰጣጥ

1. የተግባርና የፅሁፍ ፈተና የቅጥርና ዕድገት ኮሚቴው በሚመርጣቸው የሚመለከታቸው ባላሙያዎች ጥያቄ እንዲያወጡ ተደርጎ ፈተና ይሰጣል፡፡ ፈተናውም በተቻለ መጠን በዕለቱ ታርሞ ይጠናቀቃል፡፡
2. ማንኛውም ተወዳዳሪ ከሚሰጡት ፈተናዎች አንዱን ካልወሰደ ለዚያ ፈተና ውጤት ዜሮ እንዳገኘ ይቆጠራል፡፡
3. የተሰጠው ፈተና ውጤት የሚታረመው የዕድገት ኮሚቴ ወይም ተወካዮች ባሉበት ይሆናል፡፡
4. ፈተና ከተሰጠ ከሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ኮሚቴው የውሳኔ ሀሳቡን ለሚያጸድቀው አካል አቅርቦ እድገቱ እንዲጸድቅ ይደረጋል፡፡

ሐ. ከድርጅቱ ውጭ የሚሰጥ ፈተና

1. ለተወሰኑ የሙያ መስኮች ለመፈተን ፈቃድ ለተሰጣቸው ተቋማት ይሆናል፡፡
2. የፅሁፍና የተግባር ፈተና ተፈትኖ ግማሽና ከግማሽ በላይ ውጤት ያመጣ ወይም ያመጡ ተወዳዳሪዎች ወደቀጣዩ የደረጃ ዕድገት ውድድር ይሸጋገራሉ፡፡

መ. ለትምህርት ዝግጅት ማስረጃ

1. ለስራ መደቡ የተጠየቁትን ዝቅተኛ የትምህርት መስፈርት ያሟላ ተወዳዳሪ ለትምህርት ዝግጅት የተሰጠውን ሙሉ ነጥብ ያገኛል፡፡ ከተጠየቁት መስፈርቶች በላይ የሚቀርብ የትምህርት ዝግጅት ከላይ የተጠቀሰው ተጨማሪ ነጥብ አይሰጠውም፡፡
2. የትምህርት ዘመኑን ሙሉ ጊዜ ተከታትሎ ካላለፈ የተጠቀሰውን የትምህርት ደረጃ እንዳጠናቀቀ አይቆጠርም፡፡

ሠ. የስራ ልምድ

የሥራ ልምድ ማለት ሠራተኛው በድርጅቱ ውስጥ እና ከድርጅቱ ውጭ የሠራባቸው ህጋዊ የሆኑ እና የስራ ግብር የተከፈለባቸውን ልምዶች ያጠቃልላል፡፡ በመሰረተ ሃሳቡ ሰራተኛው በሚወዳደርበት ቦታ ወይም ተመሳሳይ ሥራ ለመለማመድ ከመቆየቱና ከመሥራቱ የተነሳ የሚገኘው የአሰራር ልምድና ዘዴ ለስራው ቅልጥፍና ይረዳል የሚል ግምት ስላለና ሥራውን ተረክቦ ለመስራት የሚያስችል ችሎታ አለው በሚል ሲሆን፣ የሥራ ልምድ ቀጥታ አግባብነት ያለውና በተዛዋዋሪ አግባብነት ያለው በሚል ይከፈላሉ፡፡

1. ቀጥተኛ አግባብነት ያለው የሥራ ልምድ ማለት በቀጥታ ከሚመለከተው ሥራ ጋር ግንኙነት ያለው ማለት ነው፡፡
2. በተዘዋዋሪ አግባብነት ያለው ልምድ ማለት ከስራው ጋር በቀጥተኛ ግንኙነት ሳይኖረው በተዛዋዋሪ የሚመሳሰል ማለት ነው፡፡
3. ድርጅቱ በእያንዳንዱ የሥራ መደብ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ የሥራ ልምድን የሚገልፅ ዝርዝር ከድርጅቱ የሰው ሃይል መዋቅር ጋር ተያይዞ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ ቅጁንም ለመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር ይሰጣል፡፡
4. ነጥብ አሰጣጥ
4.1. ቀጥተኛ አግባብነት ላለው የሥራ ልምድ ለእያንዳንዱ አመት አንድ ነጥብ ይሰጣል፡፡
4.2. ለተዘዋዋሪ አግባብነት ላለው የሥራ ልምድ ለእያንዳንዱ አመት 0.5 ነጥብ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን አጠቃላይ ውጤቱ ለስራ ልምድ ከተሰጠው ነጥብ አይበልጥም፡፡

ረ. የስራ አፈፃፀም ምዘና

  • የሚያገኘው ነጥብ የተቀናጀ የሥራ አፈፃፀም የ2 (ሁለት) ጊዜ ወይም የአንድ ዓመት ምዘና
    • አማካኝ x 40 ÷ 100 = እንዲመዘግብለት ይደረጋል፡፡
  • ከተቀጠረ ስድስት ወርና ከዚያ በላይ የሆነው ነገር ግን በወጣው የደረጃ ዕድገት በቂ ተወዳዳሪ ሳይገኝ ቀርቶ እንዲወዳደር የተፈቀደለት ሠራተኛ በስድስት ወሩ የተሞላለት ወይም የአንድ ጊዜ ምዘና ብቻ ይያዝለታል፡፡

ሰ. የአገልግሎት ዘመን

  • አንድ ሠራተኛ በድርጅቱ ውስጥ ላለው የአገልግሎት ዘመን ወይም ቆይታ የሚሰጥ ነጥብ ነው፡፡
  • የአገልግሎት ዘመን ነጥብ አሰጣጥ ለክፍት የስራ መደቡ ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች መካከል ረዥም ጊዜ አገልግሎት ያለው ሙሉ ነጥብ የሚያገኝ ሲሆን ሌሎች በእዚህ ስሌት እየተካፈለ ነጥብ የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡

ሸ. የግል ማህደር ጥራት

1. የማህደር ጥራት ነጥብ አሰጣጥ እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

ተ.ቁ የቅጣት ሪከርድ ከ10% የሚሰጥ ነጥብ
1 ምንም ዓይነት የዲስፕሊን ጥፋት ሪከርድ የሌለበት 10%
2 በውድድር ዓመት ውስጥ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው 8%
3 በውድድር ዓመት ውስጥ እስከ10 ቀን ደመወዝ ቅጣት የተሰጠው 6%
4 በውድድር ዓመት ውስጥ ከ11 እስከ 20 ቀን ደመወዝ ቅጣት የተሰጠው 4%
5 በውድድር ዓመት ውስጥ ከ21 እስከ 30 ቀን ደመወዝ ቅጣጥ የተሰጠው 2%
6 በውድድር ዓመት ውስጥ ከ30 ቀናት በላይ ቅጣት እርምጃ የተወሰደበት ከውድድር ውጭ ይሆናል፡፡ 0%

2. በውድድር በጀት ዓመት ውስጥ ማለት ውድድሩ ከሚካሄድበት ጊዜ በፊት የሚገኝ ሁለት የስራ አፈጻጸም የተሞላበት በጀት ዓመት ነው፡፡

3. ለስራ መደቡ የተጠየቀውን የትምህርት ማስረጃ ያሟሉ አመልካቾች ለትምህርት የተሰጠውን ሙሉ ነጥብ ያገኛሉ፡፡

4. ስልጠና ለስራ መደቡ በፋብሪካው በኩል የሚሰጠውን ስልጠና ብቻ የሚመለከት ሲሆን ይህን ስልጠና ለወሰዱ ሙሉ ነጥብ የሚያገኙ ይሆናል፡፡

13.8 ዝውውር

13.8.1 የዝውውር አፈጻጸም

1. ዝውውር ማለት አንድ ሠራተኛ ከአንድ የስራ መደብ ፣ ክፍል ፣ ፈረቃ ወይም ከዋናው መ/ቤት ወደ ቅርንጫፍ/ከቅርንጫፍ ወደ ዋናው መ/ቤት/ ሠራተኛው የያዘው ደመወዝና ደረጃ እንደተጠበቀ ሆኖ ወደ ሌላ ተመሳሳይ እና ተዛማጅ የስራ መደብ ፣ ደረጃ ፣ የሥራ ቦታ በማዛወር ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት የድርጅቱን የሥራ ውጤት ለማሻሻል ምርታነማነትን ከፍ ለማድረግ የሚፈፀም ተግባር ነው፡፡

2. ድርጅቱ የሠራተኛውን የሥራ ደረጃን ጠብቆ የሚያገኘውን ደመወዝ እንደያዘ አዛውሮ ሊያሰራው ይችላል፡፡

3. ሠራተኛው ከሥራ ጋር ባልተገናኘ ህመም ምክንያት በህክምና ቦርድ በውሉ ከተመለከተው የተለዬ ስራ እንዲሰራ ሲያዝ አሰሪው ደመወዙን ሳይቀንስ ወደ ሌላ አመቺ የሥራ ቦታ ሊያዛውረው ይችላል፡፡

4. ከአንድ የስራ መደብ ወደ ሌላ የሥራ መደብ የሚዛወር ሠራተኛ ከቀድሞ የስራ መደብ የሚያገኘው ተመላሽ ሆኖ ለአዲሱ የስራ መደብ የሚሰጠው የስራ ልብስና የአደጋ መከላከያ ያገኛል፡፡

5. የዝውውር ውሳኔ ደርሶት ቅሬታ ያለው ሠራተኛ ቅሬታውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ የሠራተኛው የወደፊት ዕድገት ለማደናቀፍ በሚችል ሁኔታ ዝውውር እንዲፈፀም አያደርግም፡፡

6. ማንኛውም የሠው ኃብት መጠይቅ የቀረበበት ክፍት የስራ መደብ እድገት ከመካሄዱ በፊት በዝውውር ይታያል፡፡ ሆኖም የእድገት ማስታወቂያ ከወጣ በኋላ የሚቀርብ የዝውውር ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፡፡

7. የሥራ መደቡ ካልታጠፈ በሙከራ ላይ ያለ ሠራተኛ ወደ ሌላ የስራ መደብ ሊዛወር አይችልም፡፡

8. ዝውውር የተጠየቀለት ሠራተኛ በመጣራት ላይ የሚገኝና ያልተወሰነ የዲሲፕሊን ክስ ወይም የገንዘብና የንብረት ጉድለት የሌለበት መሆን አለበት፡፡

9. ዋስትና በሚጠይቁ የስራ መደቦች ላይ የሚዛወረው ሠራተኛ ዋስ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

10. ማንኛውም ዝውውር በድርጅቱ የሥልጣን ውክልና መሰረት ይፈፀማል፡፡

11. በአንድ መምሪያ ውስጥ የሚደረግ የስራ ዝውውር እስከ ደረጃ 11 ድረስ ሠራተኛው በሚሰራበት የስራ ክፍል ወይም መምሪያ አቅራቢነት በሰው ኃይል ልማትና አስተዳደር የሚፈጸም ይሆናል፡፡

12. ዝውውሩ ከአንድ መምሪያ ወይም አገልግሎት ወደ ሌላ መምሪያ ወይም አገልግሎት ሲሆን፣ የመምሪያዎች ወይም የአገልግሎቶች አስተያየት ወይም ስምምነት እየተጠየቀ እስከ ደረጃ 11 ድረስ በሰው ኃይል ልማትና አስተዳደር መምሪያ ስራ አስኪያጅ ይፈፀማል፡፡ ከደረጃ 11 በላይ ከሆነ ለድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ በሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር መምሪያ ይፈጸማል፡፡

13.8.2 የቋሚ ዝውውር አፈጻጸም

1. ሠራተኛው የሚሰጠው አገልግሎት አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት ከአንድ የስራ ክፍል ወይም የስራ መደብ ወደሌላ የስራ ክፍል ወይም የስራ መደብ በቋሚነት ተዛውሮ እንዲሰራ ይደረጋል፡፡

2. ቋሚ ዝውውር ከስድስት ወር በላይ የሚደረግ ዝውውር ሆኖ ክፍት የስራ መደብ ሲፈጠር ወይንም በስራ አስፈላጊነት የሚደረግ ዝውውር ነው፡፡

3. በድርጅቱ ውስጥ በቋሚነት ተመድቦ ሲሰራ የነበረ ሠራተኛ የነበረበት የስራ ክፍል ቢዘጋ ወይም አዲስ የስራ ክፍል ቢከፈት በውስጥ ተመሳሳይ ደረጃና የስራ ባህሪይ ወዳለበት ቦታ አዛውሮ ማሰራት ይቻላል፡፡

4. ድርጅቱ በቋሚነት ለሚዛወር ሠራተኛ አስቀድሞ የዝውውር ትዕዛዝ በደብዳቤ ይገልጽለታል፡፡ በደብዳቤውም ላይ የዝውውሩ ዓይነት ፣ የተዛወረበት ቦታ ፣ ለስራ መደቡ የሚከፈለው ደመወዝ መጠን እና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችም ካሉ ተዘርዝሮ ይገለጽለታል፡፡

5. ቋሚ ዝውውር ሠራተኛው በመጀመሪያ በሚቀጠርበት ወቅት ግዴታ እንዲገባ ቢደረግም በዝውውር የሚመደብበት ቦታ ለጤናው ተስማሚ መሆኑ ከግምት ገብቶ የሚፈጸም ይሆናል፡፡ ሠራተኛው በዝውውሩ ቅር ከተሰኘ የዝውውሩ ትዕዛዝ በደረሰው በ02/ሁለት/ የስራ ቀናት ውስጥ ቅሬታውን በጽሁፍ ለወሰነው አካል ማቅረብ አለበት፡፡ የሚሰጠው ውሳኔ ካላረካው አዲስ በተዛወረበት ቦታ ሆኖ ቅሬታውን ለሚመለከተው የድርጅቱ የበላይ አካል ማቅረብ ይችላል፡፡

6. በቋሚ ዝውውር ከአንድ የስራ መደብ ወደሌላ የስራ መደብ የሚመደብ ሠራተኛ ቀድሞ ያገኝ የነበረው ደመወዝና የሥራ ደረጃ አይቀነስበትም፡፡ እንዲሁም የሚዛወርበት ቦታ /የሥራ መደብ/ ላይ ያሉ ጥቅማ ጥቅሞች ሁሉ ያገኛል፡፡

7. አንድ ሠራተኛ ከነበረበት ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በድርጀቱ ትዕዛዝ ሲዛወር ዝውውሩ ወጪ የሚያስከትል ከሆነ ለራሱ ፣ ለቤተሰቡና ለጓዙ መጓጓዣ ድርጅቱ መኪና ያቀርባል፡፡ ወይም ሠራተኛው ከነበረበት ቦታ ከተነሳበት ቀን ጀምሮ ለአዲስ የሥራ መደብ ከሚገኝበት ቦታ እስኪደርስ የውሎ አበል ፣ ለቤተሰቡና ለንብረቱ የመጓጓዣ ወጪ ይከፍለዋል፡፡ ይህ ወጪ በድርጅቱ ተመሳሳይ የስራ ቦታ ውስጥ የሚደረግ የሥራ ዝውውርን አይመለከትም፡፡

8. ማንኛውም ዝውውር ከመፈፀሙ በፊት ሠራተኛው ሥራውንና በእጁ የሚገኘውን ንብረት በቦታው ለተመደበው ወይም ለቅርብ ኃላፊው በጽሁፍ ያስረክባል፡፡ ስለሥራው የተፈፀመውንና በእቅድ ላይ ያለውን በዝርዝር በጽሁፍ ለተረካቢው ሲያስተላልፍ በግልባጭ ለሚመለከተው ክፍል ወይም አገልግሎት ኃላፊ ያሳውቃል፡፡

9. ዝውውሩ በውድድር የሚፈጸም ሲሆን እና በአንድ ስራ መደብ ላይ ከአንድ በላይ የዝውውር አመልካቾች ሲኖሩ በዕድገት መስፈርት የሚታይ ሆኖ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የዝውውር ሂደቱንም የድርጅቱ ቅጥርና ዕድገት ኮሚቴ እንዲያየው ሊደረግ ይችላል፡፡

10. ሠራተኛ ከአንድ የስራ መደብ ወደ ሌላ የስራ መደብ በቋሚነት ሲዛወር የሚመለከተው አካል በግልባጭ እንዲያውቀው ይደረጋል፡፡

13.8.3 ጊዜያዊ ዝውውር አፈፃፀም

1. ጊዜያዊ ዝውውር የሚፈፀመው ቢበዛ ለ3 /ሶስት/ ወር ብቻ ይሆናል፡፡ ሆኖም አስገዳጅ ሁኔታ ሲፈጠር ለተጨማሪ ሶስት ወር ብቻ ሊራዘም ይችላል፡፡

2. አንድ ሠራተኛ በጊዜያዊነት እንዲዛወር ሲወሰን የሚዛወርበትን ቦታና የሥራ መደብ ተጠቅሶ ደብዳቤ ይሰጠዋል፡፡ ዝውውሩም ቀድሞ ያገኛቸው የነበሩ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ደመወዙንና የሥራ ደረጃውን አይቀንስም፡፡

3. ስድስት ወር እና ከዚያም በላይ በጊዜያዊነት የሚዛወር ሠራተኛ የስራ አፈጻጸም ምዘና በትውስት ወስዶ በሚያሰራው የስራ ክፍል አማካኝነት ተሞልቶ ሠራተኛው ለሚሰራበት ዋና ክፍል እንዲተላለፍ ይደረጋል፡፡

4. በጊዜያዊነት የተዛወረ ሰራተኛ በተዛወረበት የስራ ክፍል ጥፋት ቢፈጽም በጊዜያዊነት የወሰደው የስራ ክፍል ተገቢ ማስረጃዎችን አደራጅቶ ለሰው ኃብት ልማ/አስ/ጠቅ/አገ/መምሪያ በወቅቱ የማስተላለፍ ግዴታ አለበት፡፡

5. በጊዜያዊነት የተዛወረ ሠራተኛ ጊዜውን አጠናቆ ወደቀድሞ የስራ መደቡ ሲመለስ በነበረበት የስራ ደረጃና ሙያ ተመድቦ እንዲሰራ ይደረጋል፡፡

6. አንድ ነፍሰ ጡር ሠራተኛ የምትሰራው ሥራ ለጤናዋ የማይመች መሆኑ ከህጋዊ የህክምና ተቋም ማስረጃ ካቀረበች ባቀረበችው ማስረጃ መሠረት ችግሩ እስኪወገድላት በጊዜያዊነት ዝውውር ሊፈጸምላት ይችላል፡፡

13.8.4 በድርጅቱ አነሳሽነት የሚፈፀም ዝውውር

1. ድርጅቱ ክፍት የሥራ መደቦችን አሟልቶ ለማሠራት ፣ የሰው ኃብት አጠቃቀም ሥርዓቱን ለማሻሻል ፣ ከፍተኛ የሥራ ጫናን ለማቃለል ወይም በሌላ ተመሳሳይ ምክንያት ሠራተኛውን ከአንድ የሥራ መደብ ወደ ሌላ ወይም ከአንድ የሥራ ቦታ ወደ ሌላ አዛውሮ የማሠራት መብት አለው፡፡

2. ሠራተኛው በድርጅቱ አነሳሽነት በቋሚ ዝውውር ከአንድ የስራ መደብ ወይም ቦታ ወደ ሌላ የስራ መደብ ወይም ቦታ ሲዛወር ቀድሞ ያገኝ የነበረው ደመወዝ አይቀነስበትም፡፡

3. ሠራተኛው የተሰጠውን ኃላፊነት ለመፈፀም ፈቃደኛ ሆኖ ካልተገኘ በዚህ ሕብረት ስምምነት ወይም በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ 1156/2011 መሠረት አስፈላጊውን የሥነ ሥርዓት እርምጃ እንዲወሰድበት ይደረጋል፡፡

13.8.5 በሠራተኛ አነሳሽነት የሚደረግ ዝውውር

1. ሠራተኞች ችሎታቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ወይም የተሻለ የወደፊት የማደግ ዕድል ለማግኘት ወይም የግል ወይም የጤንነት ችግርን ወዘተ… ለማቃለል በተመሳሳይ ደረጃ ወይም ከደረጃ ዝቅ ብሎ ወደ አንድ የተለየ ሥራ ወይም የሥራ ቦታ ተዛውረው ለመሥራት ጥያቄ ማቅረብ ይችላሉ፡፡

2. ማንኛውም በተመሳሳይ ደረጃ ወይም ከደረጃ ዝቅ ብሎ ለመስራት ከሠራተኛው ለሚቀርብ ጥያቄ በቂና አሳማኝ የሆነ ማስረጃ ማቅረብ እና በድርጅቱ ሊታመንበት ይገባል፡፡ እንዲሁም ከደረጃ ዝቅ ብሎ ለመዛወር የሚፈልግ ሠራተኛ ደመወዙና ጥቅማ ጥቅሙ ተዛውሮ እንዲሰራ በተመደበበት የስራ መደብ የተፈቀደው ይሆናል፡፡ ሆኖም ያቀረበው ማስረጃ አሳማኝ ካልሆነ ድርጅቱ ጥያቄውን ውድቅ ሊያደርገው ይችላል፡፡

3. ለጐንዮሽ ዝውውር የሚቀርብ ጥያቄ ለሰው ኃብት ልማት አስ/ጠቅ/አገልግሎት መምሪያ መቅረብ አለበት፡፡ በዝውውር ጥያቄ አፈፃፀም የስራ መደቡ ክፍት መሆኑን ፣ ችሎታን ወይም የስራ መደቡ የመመዘኛ መስፈርት ማሟላቱን ፣ የስራ አፈፃፀም ምዘናን ፣ የአገልግሎት ዘመንና ለሚፈለገው ሥራ ያለው አግባብነት ያለው የሥራ ልምድ በማረጋገጥ የሚሰራበትን የሥራ ክፍል እና የሚዛወርበትን የስራ ክፍል በጽሁፍ ሊጠይቅ ይችላል፡፡

4. የሠራተኛው የዝውውር ጥያቄ በድርጅቱ አሠራር ላይ ተጽዕኖ የማያሳድር ሆኖ ከተገኘና የሚቀርበው የጤንነት ችግር ከህጋዊ የሕክምና ተቋም በቦርድ የጸደቀ ማስረጃ ከቀረበ በዋና ስራ አስኪያጅ ወይም በተወካይ ሲጸድቅ ዝውውሩ ሊፈጸም ይችላል፡፡

5. ለሚዛወረው ሠራተኛ የዝውውር ምደባ ደብዳቤ ይሰጠዋል፡፡የሚመለከታቸው አካላትም እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡

6. አንድ ሠራተኛ የውስጥ ዝውውር ጥያቄ ሊያቀርብ የሚችለው በደረጃ እድገት በተመደበበት የስራ መደብ ላይ ቢያንስ አንድ ዓመት የሠራ ከሆነ ነው፡፡

13.9 የውክልና አሰራርና ተተኪን ስለማፍራት

13.9.1 ተወካይ ሠራተኛ ስለመመደብ

1. ተወካይ ሠራተኛ የሚመደበው አንድ የስራ መደብ ክፍት ሲሆንና ቋሚ ሠራተኛ እስኪመደብ ወይም አንድ ሠራተኛ ለተወሰነ ጊዜ በስራ ጉዳይ ፣ በህመም ዕረፍት ፣ በዓመት ዕረፍትና በመሳሰሉት ምክንያት በመደበኛ ስራው ላይ መገኘት በማይችልበት ጊዜና በቦታው ሌላ ሠራተኛ ለስራ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የስራ መደቡን ለመሸፈን ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ከፍ ወዳለ ወይም እኩል ለሆነ የስራ መደብ ነው፡፡

2. በተወካይነት የሚመደበው ሠራተኛ ለክፍት ቦታው ተመጣጣኝ ችሎታና የስራ ልምድ ያለው መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡ እንዲህ አይነቱ ሠራተኛ የማይገኝ ከሆነ ወይም ተወካይ ሠራተኛ መመደብ አስፈላጊ ካልሆነ የስራ መደቡ የሚገኝበት የስራ ኃላፊ ስራውን ደርቦ እንዲሰራ ይደረጋል፡፡

3. ተወካይ ሠራተኛ የሚመደበው የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ በቅድሚያ በማስፈቀድ ሲሆን ለተወካዩ በደብዳቤ ይገለፃል፡፡

4. በተወካይነት ለተመደበ ሠራተኛ የተወከለበትን የስራ መደብ ደመወዝ 40% ውክልና አበል ክፍያ የሚያገኝ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ከብር 1000.00 (አንድ ሽህ ብር) መብለጥ የለበትም፡፡

5. በውክልና ተመድቦ ለሚሰራ ሠራተኛ ክፍያ የሚፈጸመው በተከታተይ ለ26 የስራ ቀናት እና ከዚያ በላይ መስራቱ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ለአንድ የስራ መደብ አንድን ሠራተኛ ከስድስት ወር በላይ በውክል ማሰራት አይቻልም፡፡ ሆኖም ግን እንደአስፈላጊነቱ ታይቶ ለድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ቀርቦ ይወሰናል፡፡

6. ተወካይ ሠራተኛ የራሱን ሥራ እየሰራ የተወከለበትን ስራ ደርቦ የሚሰራ ሠራተኛ ነው፡፡ ሆኖም ግን እንደስራው ባህሪ ሁለት ስራዎች ደርቦ መስራት የማይችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም የተወከለበትን ስራ ብቻ እንዲሰራ ይደረጋል፡፡

7. በውክልና በተመደበበት የስራ መደብ ላይ በዚህ አንቀጽ ተ.ቁ 5 ለተገለጸው ቀናት ተወክሎ የሚሰራ ማንኛውም ሠራተኛ የተወካይነት አበል የማግኘት መብት አለው፡፡

13.9.2 ተተኪን ስለማፍራት

1. ተተኪ ማለት አስቀድሞ በቁልፍ የስራ መደብ ተይዞ ከውስጥ ሠራተኞች በመመልመል በሥራ መደቡ ላይ የተመደበው ሠራተኛ በስራው ላይ እያለ የሚደረግ ሠራተኛን የማብቃት ሥራ ነው፡፡ ይህም ድርጅቱ የሚያጋጥመውን የሰው ኃብት ፍልሰትና ክፍተት ለመቋቋም የሚያስችለው ሆኖ አንድ ሠራተኛ ሲለቅ ያለምንም ችግር ለመተካት እንዲያስችል ነው፡፡

2. የድርጅቱ ሠራተኞች በጡረታ ፣ በደረጃ ዕድገት ፣ በዝውውርና በስንብት ድርጅቱን በመልቀቅ ወዘተ…. መደበኛ ሥራቸውን ወይም ድርጅቱን ለቀው ከመሄዳቸው በፊት በቦታው የሚመጥንና የሚተካቸውን ሠራተኛ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡

3. ድርጅቱ ለቁልፍ ለስራ መደቡ የሚመጥን ከውስጥ ሠራተኞች መካከል ተተኪ ሠራተኛ ካላገኘ ከውጭ በመቅጠር በተኪነት መያዝ ይቻላል፡፡

4. የተተኪ ምደባ በአሰራር መሰረት የሚፈፅም ሆኖ በኮሚቴ የሚሰራ ከሆነ በተተኪ ኮሚቴው ውስጥ ከመሰረታዊ ሠራተኛ ማህበር አንድ አባል ይመደባል፡፡

አንቀጽ አስራ አራት

የሥራ ሠዓት ፣ የህዝብ በዓላት ፣ ትርፍ ሰዓትና የሳምንት የዕረፍት ቀን

14.1 የስራ ሰአት

1. መደበኛ የሥራ ሰዓት በቀን ከ8 ሰዓት ወይም በሳምንት ከ48 ሰዓት አይበልጥም፡፡

2. ለፈረቃ ሠራተኞች የፈረቃው የ30 ደቂቃ የምሳ(የእራት) ጊዜ ይኖራቸዋል፡፡

3. በማንኛውም የስራ ወይም በሳምንት የዕረፍት ቀን ወይም በህዝብ በዓላት ቀን ቀጥሎ ለተመለከቱት አገልግሎት ሰጪ ክፍል ሠራተኞች አሰሪው እንደ አስፈላጊነቱ በሥራ ላይ እንዲገኙ ሊያደረግ ይችላል፡፡

  • ሰርቪስ ሹፌሮች
  • የጥበቃ ሠራተኞች
  • የቴክኒክ ክፍል ሠራተኞች
  • የውሃ አገልግሎትና የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች

4. ሠራተኛ በፅሁፍ ከፈረቃ ወደ ፈረቃ ወይም ከፈረቃ ወደ መደበኛ ፈረቃ ሲመደብ የስራ ሰዓቱ ተመድቦ በሚሰራበት የስራ ሰዓት ይሆናል፡፡

14.2 የህዝብ በዓላት

1. በሀገራችን አግባብ ባላቸው ህጎች የሚከበሩ የህዝብ በዓላት ቀን ሠራተኛው በስራ ላይ እንደተገኘ ወይም እንደሰራ ተቆጥሮ ደመወዝ የሚከፈልባቸው ይሆናል፡፡

2. በዚህ አንቀጽ ተ.ቁ 1 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት በሚያወጣቸው መመሪያዎች መሰረት ስራ በማይኖርባቸው ቀናት ሠራተኛው ደመወዝ ይከፈልዋል፡፡

14.3 የትርፍ ሰዓት ሥራ

1. ስለትርፍ ሰአት ስራ ፣ የትርፍ ሰአት ስራ የሚፈቀድባቸው ሁኔታዎች እና አከፋፈል በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ከአንቀጽ 66-68 በተዘረዘረው መሰረት ይፈጸማል፡፡

2. ትርፍ ሰአት እንዲሰራ የታዘዘ ሠራተኛ ለመስራት የማይችልበትን ሁኔታ ለቅርብ የስራ ኃላፊው በቅድሚያ በጽሁፍ ካሳወቀው በስራ ላይ የመገኘት ግዴታ የለበትም፡፡

3. የትርፍ ሰአት ክፍያ የሚፈፀመው ከ30 ደቂቃ በላይ ለተሰራ ስራ ብቻ ነው፡፡

4. ነፍሰጡር መሆናቸው የታወቀ ፣ በቀላል ስራ የተመደቡ ሠራተኞች ትርፍ ሰአት እንዲሰሩ አይገደዱም፡፡

14.4 የሳምንት ዕረፍት ቀን

1. የሳምንት ዕረፍት ቀን እሁድ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በአንቀፅ 14.1 ተ.ቁ 3 ለተዘረዘሩት የስራ መደቦች ድርጅቱ እሁድ ስራ እንዲሆን ከወሰነ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀፅ 70 መሰረት ከሳምንት የስራ ቀኖች አንዱን መርጦ የእረፍት ቀን እንዲሆን ያደርጋል፡፡ አፈፃፀሙን ድርጅቱና ሰራተኛ ማህበሩ በጋራ ጥናት በማድረግ ይወሰናል፡፡

አንቀጽ አስራ አምስት

የደመወዝና ልዩ ልዩ ክፍያዎች የደመወዝ ጭማሪና ማነነቃቂያ ክፍያ

15.1 ደመወዝ

1. ደመወዝ ማለት አንድ ሠራተኛ በስራ ውሉ መሰረት ለሚያከናውነው ስራ የሚከፈለው መደበኛ ክፍያ ነው፡፡

2. ማንኛውም በድርጅቱ የሚሰራ ሠራተኛ ደመወዝ የሚወሰነውና የሚከፈለው በፋብሪካው በጸደቀው የደመወዝ ስኬል እና በስራ ውሉ ላይ በተደረገው ስምምነት መሰረት ይሆናል፡፡ የፋብሪካውን ዓመታዊ የስራ እቅድ ስኬት መሰረት በማድረግ ሠራተኞች ከአንድ የደመወዝ ዕርከን ወደሚቀጥለው የደመወዝ እርከን የሚያድጉት በስራ እቅድ አፈጻጸም ምዘና ውጤት ነው፡፡

3. ማንኛውም ሠራተኛ በሠራበት ጊዜ መጠን በሥራ ውሉ እና ለስራ መደቡ በተቀመጠው የደመወዝ ስኬል መሰረት ደመወዝ ይከፈለዋል፡፡

4. የሠራተኛው ደመወዝ በድርጅቱ በታተመ የደመወዝ መክፈያ ሰነድ (ፔይሮል) ላይ ወይም በሠራተኞች የግል የባንክ ሂሳብ ቁጥር ይከፈላል፡፡

5. ለተወሰነ ጊዜ የተቀጠሩ እና ላልተወሰነ ጊዜ የሚቀጠሩ ሠራተኞች የደመወዝ መክፈያ ሰነድ የተለየ ይሆናል፡፡

6. የደመወዝ መክፈያ ሰነዱ የሠራተኛው ስም ፣ የሥራ ክፍሉ ፣ የደመወዙ መጠን ፣ የገቢ ግብር ፣ የጡረታ መዋጮ ፣ በሠራተኛው የተወሰደ ብድር ካለ ቅናሽ ፣ የቅጣት ተቀናሽ እና ሌሎች አግባብነት ያላቸው ቅንስናሾች እና ለሠራተኛው የሚደርስ የተጣራ ክፍያን በዝርዝር የሚያሳይ መሆን ይኖርበታል፡፡

7. ደመወዝ በግል የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ የተደረገላቸውም ሆነ ሌሎች በደመወዝ መክፈያ ሰነድ ፈርመው የሚወስዱ ሠራተኞች በፋይናንስ መምሪያ በኩል የደመወዛቸውን መጠንና ሌሎች ተቀናናሾችን የያዘ የማረጋገጫ ሰነድ /Payment Slip/ ይሰጣቸዋል፡፡

8. ደመወዝ የሚፈጸመው በፔሮል ወይም ደመወዝ መክፈያ ሰነድ ከሆነ ሠራተኛው ደመወዙን ሲቀበል በተዘጋጀው የደመወዝ መክፈያ ሰነድ ላይ መፈረም ይኖርበታል፡፡

9. የሠራተኛው ደመወዝ ሲዘጋጅ የተቆረጠ የገቢ ግብር ፣ የጡረታ መዋጮ ፣ በሠራተኛው የተወሰደ ብድር እና ሌሎች ቅንስናሾች በወቅቱ ለሚመለከተው አካል መከፈል ወይም ገቢ መደረግ አለባቸው፡፡

10. የወር ደመወዝ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በወር መጨረሻ በ30 ይከፈላል፡፡

11. የወር ደመወዝ የሚከፈልበት ቀን በሳምንት እረፍት ቀን ወይም በህዝብ በዓላት ቀን ከሆነ ከመደበኛ የክፍያ ቀን አስቀድሞ ይከፈላል፡፡

12. ደመወዝ የሚከፈለው በቀጥታ ለሠራተኛው ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ህጋዊ ምክንያቶች ሠራተኛው ቀርቦ መቀበል ካልቻለ የሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር መምሪያ ባዘጋጀው ቅፅ መሰረት ሠራተኛው በፅሁፍ ለሚወከለው ሠራተኛ ተረጋግጦ ሊከፈለው ይችላል፡፡

13. በህግ ፣ በሠራተኛው የፅሁፍ ስምምነት ፣ በስራ ደንብ ወይም በፍ/ቤት ትዕዛዝ ካልሆነ በስተቀር የማንኛውም ሠራተኛ ደመወዝ አይዝም ፣ አይቆረጥም፡፡

14. በአንድ ጊዜ ከሠራተኛው ደመወዝ ላይ በዕዳ ሊቆረጥ የሚችለው የገንዘብ መጠን ከወር ደመወዙ 1/3ኛ መብለጥ የለበትም፡፡

15.2 የቅድሚያ ክፍያ

ሠራተኛው ከደመወዙ ቅድሚያ ክፍያ/አድቫንስ/ ሲፈልግ የደመወዙን 1/3ኛ በቅድሚያ እንዲሰጠው በጽሁፍ መጠየቅ ይችላል፡፡ ይህም በድርጅቱ መረጋገጥና መፈቀድ ይኖርበታል፡፡

15.3 የወሎ አበል

1. ማንኛውም ሰራተኛ ለድርጅቱ ሥራ ጉዳይ ድርጅቱ ካላበት ከተማ ውጭ ሲንቀሳቀስ የውሎ አበል ይከፈለዋል፡፡ ለዚህ ተግባር አሰሪው የትርንስፖርት አገልግሎት ካላቀረበ ለተጓዡ የትራንስፖርት ወጪውን በመንግስት ታሪፍ መሰረት በሚያቀርቡት ህጋዊ ማስረጃ ይከፈለዋል፡፡ ነገር ግን ሁኔታው የተለየና አሳማኝ ሆኖ ሲገኝ በመምሪያው ሥራ አስኪያጅ ሲፈቀድ ሰራተኛው በሚያቀርበው ህጋዊ ማስረጃ መሰረት እንዲወራረድለት ይደረጋል፡፡

2. የውሎ አበል ክፍያ እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

ተ.ቁ የወር ደመወዝ ስኬል የአንድ ቀን አበል
1 እስከ ብር 3000.00 ብር 350.00
2 ከብር 3001 - 7000.00 ብር 400.00
3 ከብር 7001 – 10,000.00 ብር 450.00
4 ከብር 10,001 – 12,000.00 ብር 500.00
5 ከብር 12,001 – በላይ ብር 600.00

3. ድርጅቱ ወቅታዊ ሁኔታን በማየት የውሎ አበሉ ተመኑን ሊያስተካክል ይችላል፡፡

4. የበረሀ አበል መንግስት በርሃ ተብለው የተያዙ ቦታዎች ለሚደረግ ጉዞ በአበሉ ላይ ተጨማሪ 30% ይከፈለዋል፡፡

5. የውጭ አገር አበል ድርጅቱ እነደወቅቱ ሁኔታ እያየ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት የሚወሰን ይሆናል፡፡

6. ማንኛውም የውሎ አበል ከ30 ቀናት በላይ መብለጥ የለበትም፡፡ ነገር ግን ከ30 ቀናት በላይ መጨመሩ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የዋና ሥራ አስኪያጅ እንደገና ታይቶ በልዩ ሁኔታ መፅደቅ ይኖርበታል፡፡

7. ምግብና መኝታ በሌላ ወገን ከተሸፈነ ለልዩ ልዩ ወጭ የአበሉን 25% ብቻ ይከፈላል፡፡

8. ማንኛውም የሚያሳድርና አበል የሚከፈልበት ጎዞ ከመደረጉ በፊት በሚመለከተው ኃላፊ መፈቀድ አለበት፡፡

9. የውሎ አበል እየተከፈለው ለሚሰራ ሠራተኛ የትርፍ ሰዓት አይከፈለውም፡፡

10. የአንድ ቀን ውሎ አበል ስሌት ለቁርስ 10% ፣ ለምሳ 25% ፣ ለእራት 25% እና ለአልጋ 40% ሲሆን አንድ ሠራተኛ ከጠዋቱ 2፡00 ሰአት በፊት ለስራ ጉዳይ ካለበት የስራ ቦታ ቢያንስ ከ40 ኪ.ሜትር በላይ ከተንቀሳቀሰ ለቁርስ የታሰበው የውሎ አበል 10% ፣ ከ6፡00 ሰአት በፊት ለስራ ጉዳይ ሄዶ የምሳ ሰአቱን በሄደበት የስራ ቦታ ያሳለፈ ለምሳ የተያዘው የውሎ አበል 25% ፣ ከምሽቱ 2፡00 ሰአት በፊት ወደ ምድብ ስራው ካልተመለሰ ለእራት የተያዘው 25% ፣ አዳሩን በሄደበት ቦታ ያሳለፈ ሠራተኛ ለአልጋ/መኝታ/ የተያዘው የውሎ አበል 40% ይከፈልዋል፡፡

11. በዚህ አንቀጽ የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጅቱ በሚገኝበት ከኮምቦልቻ ውጭ በሚገኙ አቅራቢያ ከተሞች ማለትም ደሴ እና አካባቢው ለስራ ጉዳይ የሚሄዱ ሠራተኞች የምሳ ሰአታቸውን እዛው የሚያሳልፉ ከሆነ የውሎ አበላቸው 25% ታስቦ የምሳ አበል ይከፈላቸዋል፡፡

ሀ. የቁርስ አበል የሚከፈለው ከጧቱ 1፡00 ሰዓት በፊት ጉዞ የጀመረ ወይም ከአለበት ከተማ ውጭ አድሮ ከጧቱ 2፡00 ሰዓት በኋላ የገባ ከሆነ ፣

ለ. የምሳ አበል የሚከፈልው ከቀኑ 6፡00 ሰዓት በፊት ካለበት ከተማ የወጣ ወይም ከ7፡00 ሰዓት በኋላ የተመለሰ ከሆነ፣

ሐ. አንድ ሠራተኛ ከመደበኛ የስራ ቦታው ከ50 ኪ/ሜ እና ከዚያ በላይ በሆነ ርቀት የድርጅቱን ሥራ ለማከናወን ቢታዘዝ ከጠዋቱ 1፡00 በፊትና ለስራ ወጥቶ ሥራውን በማከናወን በዕለቱ በማንኛውም ሰዓት ቢመለስ የሙሉ ቀን አበል ይከፈለዋል፡፡

መ. ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ለሥራ ከወጣ የቁርስና የምሳ አበል ብቻ ተቀንሶ ቀሪው የእራትና አልጋ አበል ሥራው ከሚወስደው ጊዜ የአበል ክፍያ ጋር ታስቦ ይከፈለዋል፡፡

ሠ. የመስክ ስራው ከአንድ ቀን በላይ የሚፈጅ ከሆነ ከፊደል ሐ- መ ድረስ የተዘረዘሩት እንደተጠበቁ ሆነው ሥራውን አጠናቆ በሚመለስበት ቀን በማንኛውም ሰዓት ቢመለስ በስራ ላይ ያሳለፋቸው ቀናት አበልና የመሳሰሉት ዕለት የሙሉ ቀን አበል ይከፈለዋል፡፡

ረ. ከላይ የተገለፀው እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ሰራተኛ ከመደበኛ የስራ ቦታው ከ50 ኪ/ሜ በታች የሆነ ርቀት የድርጅቱን ሥራ እንዲያከናውን ከታዘዘና ሰራተኛውም በሥራው ላይ የሳለፈው ጊዜ የቁርስ ወይም የራት ወይም የመኝታ አበል ወይም ድምር አበል ይከፈለዋል፡፡ ነገር ግን ሆን ብሎ ምክያት በመፍጠር መግባት በሚገባው ጊዜ ወይም ሰዓት ባለመግባት የውሎ አበል ጥቅም ያለ አግባብ ለማግኘት የሚያደርግ ሰራተኛ በህብረት ስምምነት መሰረት ይቀጣል፡፡

15.4 የካዝና ጉድለት ማካካሻ አበል

1. በድርጅቱ ውስጥ በገንዘብ ያዥነት ፣ ደመወዝ ከፋይነት እና ዕለታዊ ገንዘብ ሠብሣቢነት የሚሠራ ሠራተኛ በሥራው ፀባይ ምክንያት ሊከሰትበት የሚችለውን አነስተኛ የገንዘብ ጉድለት ታሳቢ በማድረግ የካዝና ጉድለት ማካካሻ አበል ይከፈለዋል፡፡

2. ለገንዘብ ያዥ ፣ ለደመወዝ ከፋዩ ወይም ለገንዘብ ሰብሳቢው የሚከፈለው የካዝና ጉድለት ማካካሻ አበል መጠን በወር ብር 200.00/ሁለት መቶ ብር/ ይሆናል፡፡

አንቀጽ አስራ ስድስት

ዓመታዊ የደመወዝ ጭማሪና ቦነስ

16.1 የድርጅቱ አመታዊ የደመወዝ ጭማሪና ቦነስ የሚሰጠው የድርጅቱ ሰራተኞች ለሥራ ለማነቃቃትና ድርጅቱን ትርፍማ ለማድረግ ታስቦ ሲሆን፣ የጭማሪና የቦነስ አሰጣጥም የድርጅቱን ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻጸም መሰረት ያደረገ ይሆናል፡፡

16.2 ዓመታዊ የደመወዝ ጭማሪና ቦነስ አከፋፈልን በተመለከተ ድርጅቱ በየዓመቱ በሚያወጣው የአፈጻጸም መመሪያ መሰረት በድርጅቱ የሚወሰን ይሆናል፡፡

16.3 ቦነስና ደመወዝ ጭማሪ የማይመለከታቸው ሠራተኞች

ሀ. የዓመቱ የስራ አፈፃፀማቸው ውጤት ከአጥጋቢ በታች የሆነ፣

ለ. ከዓመት ፈቃድ ፣ ከሥራ ላይ አደጋ ፣ ከወሊድ ፈቃድ ፣ ካንሰር ፣ ኮቪድ 19 ወይም በኮሮና ቫይረስ ፣ ስኳርና ከፍተኛ የደም ግፊት ካለባቸው ፣ በደማቸው ውስጥ የኤች.አይ.ቪ ከተገኘባቸውና ራሳቸውን ካሳወቁ ራሳቸውን ህሙማን በስተቀር ሁለት ወርና ከዚያ በላይ ቀሪ ያላቸው፣

ሐ. በዲሲፕሊን ግድፈት ከስራቸው የተሰናበቱ ፣

መ. የሙከራ ጊዜያቸውን ያልጨረሱ ሠራተኞች ፣

16.4 አንድ ሠራተኛ የቦነስ ክፍያ የሚያገኘው ቦነሱ በተገኘበት የሥራ ዘመን ባደረገው አስተዋፅኦ በመሆኑ የክፍያው አፈፃፀም ለሰራባቸው ጊዜ ብቻ ይሆናል፡፡ በህመም ምክንያት ከሁለት ወር በላይ በስራቸው ላይ ያልተገኙ ሰራተኞች የተቀናጀ የሥራ አፈፃፀም ምዘና ውጤታቸው የተቀናጀ የሥራ አፈፃፀም መመሪያ መሰረት አጥጋቢና ከአጥጋቢ በላይ ሆኖ ከተገኘ ለሰሩባቸው ጊዜያቶች ታስቦ ቦነስ ይሰጣቸዋል፡፡

16.5 ድርጅቱ በጥናት ላይ የተመሰረተ የማነቃቂያ ክፍያ ሊኖረውና እንደአስፈላጊነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠና ሊሻሻል ይችላል፡፡

አንቀጽ አስራ ሰባት

የደመወዝ ክፍያ ሥርዓትና የበጀት ዓመት

17.1 ድርጅቱ የሚቀጥረው ወይም የሚመድበውን ሠራተኛ በደመወዙ ስኬል መሰረት ይከፈለዋል፡፡

17.2 ድርጅቱ ላሉት የስራ መደቦች የራሱ የድርጅቱ የደመወዝ ስኬል ሥርዓት ይኖረዋል፡፡ ሆኖም ድርጅቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሠራተኞችን ከድርጅቱ ስኬል ውጭ በድርድር መቅጠር ሲያስፈልገው ይህንኑ ለማድረግ መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡

አንቀጽ አስራ ስምንት

የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ

ድርጅቱ የሠራተኞችን ጤንነት ለመጠበቅ የህክምና አገልግሎቶችን በሆስፒታሎች ፣ በጤና ጣቢያዎችና በክሊኒኮች እንዲያገኙ በማድረግ ጤናማና አምራች ሆነው ድርጅቱን ብሎም ሀገራቸውን ለማገልገል የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቻል ፡፡

በድርጅቱ ተቀጥረው የሚሰሩ የተወሰነ ጊዜ እና ያልተወሰነ ጊዜ ቅጥር ሠራተኞች ለሚያጋጥማቸው የጤና ችግር ፣ የስራ ላይ አደጋና የአካል ጉዳት የህክምና አገልግሎት ያገኛሉ፡፡

1. ድርጅቱ እየሰፋ በሚሄድበት ወቅትና የፋይናንስ አቅምን መሰረት በማድረግ እንደአስፈላጊነቱ እየታየ የራሱን የህክምና ተቋም ሊያቋቁም ይችላል፡፡

2. ድርጅቱ በአካባቢው ከሚገኙ የህክምና ተቋማት ጋር ውል በመግባት ለሠራተኞች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡

3. ድርጅቱ ውል በገባባቸው የህክምና ተቋማት ለሚሰጥ የህክምና አገልግሎት ከሠራተኛው 30% እና በፋብሪካው 70% ድርሻ አገልግሎት ወጪ በመሸፈን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ድርጅቱ የውጭ ሀገር ህክምና ወጪን አይሸፍንም፡፡

4. ሠራተኞች ከድርጅቱ የህክምና መላኪያ ቅጽ የሚመለከተው አካል በማስፈረም ይዘው በመሄድ በቅድሚያ ውል ከተገባበት ህክምና ተቋም ብቻ መታከም ይኖርባቸዋል፡፡ ድርጅቱ ውል የገባበት የህክምና ተቋም ለተጨማሪ ምርመራ ሪፈር ካላለ በስተቀር ከሌላ ህክምና ተቋም የሚመጣ የህክምና ወጪ ማስረጃ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡

5. በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 አንቀጽ 79 ተ.ቁ 5 መሰረት አንድ ሠራተኛ በዓመት ፈቃድ እያለ ቢታመምና በህክምና ተቋም እንዲተኛ ለተደረገበት ጊዜ ብቻ የዓመት ፈቃዱ ተቋርጦ የህመም ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡

6. ድርጅቱ እንደአስፈላጊነቱ የሠራተኞች የሕክምና ወጪ በዚህ አንቀጽ ተ.ቁ 3 ላይ በተገለጸው መሰረት በቀጥታ መሸፈን ወይም የሕክምና ኢንሹራንስ ሽፋን በመግዛት መሸፈን ይችላል፡፡

7. ድርጅቱ በስራ ላይ አደጋ የደረሰ ካልሆነ በስተቀር የጥርስ ማስተካከል ወይም ማስተከል ወጪን ፣ የአይን ህክምና ፣ በሀኪም ለሚታዘዝ የአይን መነጸር ፣ ጤንነትን ለማረጋገጥ ለሚደረግ የጠቅላላ ምርመራ ወጪን ፣ የውጭ ሀገር ህክምና ወጪን አይሸፍንም፡፡

8. በሥራ ቦታ ላይ ለደረሰ ወይም ከስራ ጋር በተያያዘ አደጋ እና ሕመም የህክምናውን ሙሉ ወጪ እና በአዋጅ 1156/2011 እንዲሁም በህብረት ስምምነት እና ሌሎች ተያያዥ ህጎች መሰረት የሠራተኛውን ደመወዝ ይሸፍናል፡፡

9. አንድ ሠራተኛ ለከፍተኛ ህክምና ወደአዲስ አበባ ከተላከ የደርሶ መልስ የትራንስፖርት ወጪ በድርጅቱ በሚያቀርበው ደረሰኝ መሰረት ይሸፈናል፡፡ ሠራተኛው በወቅቱ ላወጣው የህክምና ወጪ በአሰራሩ መሰረት ከሚደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ለሌሎች ተያያዥ ወጪዎች በሚቀርበው ጥያቄ መሰረት እንደሁኔታው እየታየ በድርጅቱ ድጋፍ የሚደረግበት ሁኔታ ሊመቻች ይችላል፡፡

10. ድርጅቱ ለሠራተኞች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ውል የገባበትን የህክምና ተቋም አሠራር በተመለከተ ከሠራተኞች በሚቀርብ ቅሬታ መሰረት እንዲሁም በየጊዜው ከሠራተኛ ማህበር ጋር በመመካከር ከህክምና ተቋሙ ጋር ውይይት እና አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋል፡፡

11. አንድ ሠራተኛ የዓመት ፈቃድ ላይ እያለ በድርጅቱ የስራ አካባቢ ካለ ከድርጅቱ የህክምና መላኪያ ወረቅት በመውሰድ ውል ከተገባበት ህክምና ተቋም መታከም ይኖርበታል፡፡ ሆኖም በዓመት ፈቃድ ምክንያት በስራ አካባቢ ከሌለ እና የህምክና መላኪያ ወረቅት መውሰድ የማይችልበት አካባቢ ከሆነ በሄደበት አካባቢ በሚገኝ የመንግስት ህክምና ተቋም መታከም እና የሚያቀርበው የህክምና ወጪ ደረሰኝ በአሰራሩ መሰረት ይሸፈናል፡፡

12. ሠራተኛው ካጋጠመው የህመም ሁኔታ በመነሳት ድርጅቱ ውል ከወሰደባቸው የህክምና ተቋማት ውጭ ለመታከም አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት እና ሠራተኛው ጥያቄ ሲያቀርብ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ እና ከሠራተኛ ማህበሩ ጋር በመወያየት የረዥም ጊዜ ብድር ሊመቻችለት ይችላል፡፡ ሆኖም የሚያቀርበው የህክምና ፈቃድ ተቀባይት አይኖረውም፡፡

13. የህመም ፈቃድ ህመሙ ከደረሰበት የመጀመሪያ ቀን አንስቶ ባለው አስራ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በተከታታይ ወይም በተለያዩ ጊዜያት ቢወሰድም በማንኛውም ሁኔታ ከስድስት ወር አይበልጥም፡፡ የህመም ፈቃድ ቀጥሎ በተመለከተው ሁኔታ ይሰጣል፡፡

ሀ/ ለመጀመሪያ ወር ከሙሉ ደመወዝ ክፍያ ጋር ፣

ለ/ ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት ከደወመዙ ሃምሳ በመቶ ክፍያ ጋር ፣

ሐ/ ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት ያለክፍያ፡፡

አንቀጽ አስራ ዘጠኝ

ከስራ ጋር በተያያዘ ለሚደርስ ጉዳት የሚሰጥ ህክምና

19.1 በዚህ ህብረት በስራ ላይ የሚደርስ ጉዳት ማለት በስራ ላይ የሚደርስ አደጋ ወይም በስራ ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡

19.2 አግባብ ባለው የጡረታ ህግ የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ ሠራተኛ ስራውን በማከናወን ላይ ሳለ ወይም ከስራው ጋር ግንኙነት ባለው ሁኔታ ጉዳት ሲደርስበት በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 እና በዚህ ህብረት ስምምነት ድንጋጌዎች መሰረት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

19.3 በሠራተኛው ላይ በስራ ላይ በሚደርስበት አደጋ ወይም ጉዳት እና ከስራ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ለሚደርስ ህመም ድርጅቱ ኃላፊነት አለበት፡፡

19.4 ሠራተኛው እንዲሰራ የሚጠበቅበትን የክፍሉን ስራ ሲሰራ ወይም በመደበኛ ስራው ላይ ባይሆንም እንኳን በቅርብ ኃላፊዎቹ የስራ ትእዛዝ የድርጅቱን ስራ በሚያከናውንበት ጊዜ ለሚደርስበት አደጋ ድርጅቱ ሀላፊ ነው፡፡

19.5 ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ ሆነ ብሎ በራሱ ላይ ላደረሰው ማንኛውም ጉዳት አሠሪው ኃላፊነት አይኖርበትም፡፡ በተለይም በሚከተሉት ድርጊቶች ምክንያት የሚመጣ ጉዳት ሠራተኛው በራሱ ላይ ሆነ ብሎ እንዳደረሰው ጉዳት ይቆጠራል፡፡

ሀ/ በአሠሪው አስቀድሞ በግል የተሰጡትን የደህንነት መጠበቂያ መመሪያዎች መጣስ ወይም የአደጋ መከላከያ ደንቦችን መተላለፍ ፣ ወይም

ለ/ አካሉን ወይም አዕምሮውን በሚገባ ለመቆጣጠር በማይችልበት ሁኔታ በመጠጥ ወይም በአደንዛዥ ዕፅ ሰክሮ በስራ ላይ መገኘት፡፡

19.6 አንድ ሠራተኛ በስራው ላይ እንዳለ አደጋ ከደረሰበት በሚመለከተው የህክምና ተቋም የመጨረሻ የህክምና መረጃ ሲያቀረብ ድርጅቱ በገባው የህክምና መድን ዋስት ወይም በጡረታ ህግ መሰረት የሚፈጸም ይሆናል፡፡

19.7 ድርጅቱ በስራ ላይ ለደረሰ ጉዳት ወይም አደጋ እና ህመም የመጨረሻው የህክምና መረጃ ከቀረበ በኋላ በአስር ቀናት ውስጥ ውል ለተገባበት መድን ዋስትና መላክ ይኖርበታል፡፡

19.8 በስራ ላይ ለደረሰ ጉዳት ፣ አደጋ ወይም ህመም የሚደረገው የካሳ ክፍያ መጠን የህክምና ቦርድ በሚያሳውቀው የጉዳት መጠን መሰረት ይሆናል፡፡

19.9 በስራ ላይ በደረሰ ጉዳት ፣ አደጋ ወይም ህመም ምክንያት ሰራተኛው በህክምና ላይ ሆኖ በስራ ላይ ላልተገኘባቸው ቀናት ድርጅቱ በገባው ኢንሹራንስ ውል ለሰራተኛው ደመወዝ ይከፍላል፡፡

19.10 አንድ ሠራተኛ በስራ ላይ በደረሰበት አደጋ ምክንያት ተገቢውን ህክምና ተደርጎለት እስከ መጨረሻው የማይድን ወይም ለስራው ብቁ ያለመሆኑን የሀኪሞች ቦርድ ሲያረጋግጥ በዚህ ህብረት ስምምነትና በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሰረት የሚገባውን ሁሉ ተከፍሎት ከስራ ይሰናበታል፡፡ በተጨማሪም በስራ ላይ አደጋ ደርሶባቸው በጡረታ ወይም ስንበት የስራ ውላቸው የሚቋረጥ ሰራተኞች የሁለት ወር ደመወዝ ድርጅቱ ድጎማ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን አገልግሎት ዘመኑ የሚፈቅድለት ከሆነ በጡረታ እንዲገለል ይደረጋል፡፡

19.11 አንድ ሰራተኛ የስራ ላይ አደጋ ደርሶበት ወደ ሆስፒታል እንዲሄድ በባለሙያ ሲወሰን ለትራንስፖርት ለምርመራና ለመድሀኒት መግዣ የሚሆን ገንዘብ በቅድመ ክፍያ መልክ ይሰጠዋል፡፡ ከተሰጠው ገንዘብ ውስጥ ህጋዊ ደረሰኝ ካላቀረበ ከደመወዙ ይቀነሳል፡፡ የወጣው ወጭ ከኢንሹራንስ ማስመለስ የድርጅቱ ኃላፊነት ነው፡፡

19.12 በስራ ላይ የሚመጣ ጉዳት ለደረሰበት ሠራተኛ ለሚከተሉት የህክምና አገልግሎቶች የሚያስፈልገውን ወጭ ድርጅቱ ይከፍላል፡፡

ሀ/ የጠቅላላና የልዩ የህክምና እንዲሁም የቀዶ ጥገና ህክምና ወጪዎች፣

ለ/ የሆስፒታልና የመድሀኒት ወጪዎች፣

ሐ/ የማንኛውም አስፈላጊ ሰው ሰራሽ ምትክ ወይም ተጨማሪ አካሎችና የአጥንት ጥገና ወጪዎች፡፡

19.13 ሠራተኛው ለደረሰበት ጉዳት የሚደረግለት የህክምና አገልግሎት የሚቋረጠው የህክምና ቦርድ በሚሰጠው ውሳኔ መሰረት ይሆናል፡፡

19.14 የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀፅ 108 ተራ ቁጥር 1 መሰረት ጊዜያዊ የአካል ጉዳት እስከሚወገድ ጊዜ ድረስ በየጊዜው የሚደርግ ክፍያ ድርጅቱ ከአንድ አመት ላልበለጠ ጊዜ ይከፍላል፡፡

19.15 ማንኛውም በስራ ላይ የሚመጣ ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ የሚደረገው የክፍያ መጠን በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 108 ተ.ቁ 2 መሰረት ሠራተኛው ያገኝ ከነበረው አማካይ ደመወዝ ለመጀመሪያ ሶስት ወራት ሙሉ ደመወዝ ፣ ለሚቀጥሉት ሶስት ወራት ደግሞ 75 በመቶ እንዲሁም ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ደግሞ 50 በመቶ ይሆናል፡፡

19.16 በየጊዜው የሚደረገው ክፍያ ከሚከተሉት መካከል ቀድሞ በተፈፀመው በማናቸውም ዕለት ይቆማል፡፡

ሀ/ ሠራተኛው የደረሰበት ጊዜያዊ ጉዳት የተወገደለት መሆኑ በሀኪም ሲረጋገጥ ፣

ለ/ ሠራተኛው የጉዳት የጡረታ ካሳ ወይም ዳርጎት የሚያገኝ ቀን፣

ሐ/ ሠራተኛው ሥራ መስራት ካቆመበት ዕለት ጀምሮ አስራ ሁለት ወር ሲሞላው

19.17 ማንኛውም ሠራተኛ በስራ ምክንያት በደረሰበት ጉዳት የተነሳ የሞተ እንደሆነ ለጥገኞች ክፍያ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 አንቀጽ 110 መሰረት የሚፈጸም ይሆናል፡፡

19.18 ሠራተኛው በስራ ላይ አደጋዎች ምክንያት በህክምና ላይ ባለበት ጊዜ ለሥራው ብቁ መሆን እስከተረጋገጠ ድረስ ለዕድገት መወዳደር ይችላል፡፡ ለውድድር በወጣው ማስታወቂያ ለመወዳዳደር የተመዘገበ ሠራተኛ ውድድር ከመጀመሩ በፊት የስራ አደጋ ካጋጠመው ፈተናው እስከ 21 ቀናቶች አንዲራዘምለት ይደረጋል፡፡ ሆኖም ክፍት የስራ መደቡ በአስቸኳይ መሟላት ያለበት ከሆነ ውድድሩ የሚቀጥልና መደቡ የሚሟላ ይሆናል፡፡

አንቀጽ ሃያ

በህመም ምክንያት የሚሰጥ ቀላል ሥራ

20.1 ሠራተኛው በህመም ምክንያት በሥራ ውል ውስጥ ከተመለከተው ውጭ በቋሚነት ቀላል ሥራ እንዲሰራ የሚወሰነው ድርጅቱ ውል በገባበት የህክምና ተቋም ወይም በመንግስት ሆስፒታሎች የህክምና ቦርድ ውሳኔ ነው፡፡

አንቀጽ ሃያ አንድ

ሴፍቲ ኮሚቴ

21.1 የሴፍቲ ኮሚቴ ከሠራተኛ ማህበርና ከማኔጅመንቱ የተዋቀረ ሆኖ አፈጻጸሙም የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው ደንብና መመሪያ መሰረት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የሴቶች ስብጥር እንዲኖረው ይደረጋል፡፡

21.2 ኮሚቴው የአደጋ መንስኤዎችን እያጠና የሚወገዱበትን የመፍትሄ ሀሳቦች ለዋና ሥራ አስኪያጅ በማቅረብ የድርጅቱንና የሠራተኛውን ደህንነት ይጠብቃል፡፡

21.3 የእሳት አደጋ መከላከያ መሳሪያዎችን እንዲሟሉና የድርጅቱን ንብረቶች በአግባቡ እንዲቀመጡ ሪፖርት ያቀርባል፣ ያስፈፀማል፡፡

21.4 የድርጅቱ ጠቅላላ ንፅህና መጠበቁን ይቆጣጠራል፣ የመፀዳጃ ቤቶችን፣ የሻይ ቤት ንፅህና አያያዝ ይከታታላል፡፡

21.5 ለአዲስ ተቀጣሪ ሰራተኞች ስራ ሙያ ድህንንትና ጤንነት ተገቢውን ትምህርታዊ መግለጫ በየጊዜው እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡

21.6 አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከውስጥና ከውጭ ባለሙያዎችን እየጋበዘ ስለ ሙያ ድህንነትና ጤንነት ትምህርት እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡

አንቀጽ ሃያ ሁለት

ኢንሹራንስ

22.1 አንድ ሠራተኛ ተግባሩን ፈፅሞ ከወጣ በኋላ ወደ ቤቴ ሲመለስ 1፡00 ሰዓት ወይም ተግባሩን ለመፈፀም ወደሥራ ከመግባቱ በፊት 1፡00 ሰዓት በሥራ ላይ እንዳለ ይቆጠራል፡፡ ይህም ለድርጅቱ ሥራ ጉዳይ ከቤታቸው ተጠርተው የሚመጡትን ሠራተኞች ያጠቃልላል፡፡ በማንኛውም ወቅት የድርጅቱ ሠራተኞች በማንኛውም ቦታ ለሥራ ሲንቀሳቀሱ ለሚደርስባቸው ጉዳት በኢንሹራንስ ይሸፈናል፡፡

22.2 በስራ ላይ እያለ ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ የጉዳት ሁኔታ ሶስት ምስክሮች ፈርመውበት ድርጅቱ ውል የገባበት መድን ድርጅት ጋር መረጃው ይላካል፡፡

22.3 የስራ ላይ አደጋ የደረሰበት ሠራተኛ የውሎ አበል አከፋፈል በዚህ ህብረት ስምምነት ስለውሎ አበል በተገለጸው መሰረት ይፈፀማል፡፡ የኢንሹራንስ ድርጅቱ በዚህ መሰረት የውሉ አበሉን ካልከፈለ ድርጅቱ የሚሸፍን ይሆናል፡፡ሆኖም ግን የውሉ አበሉ በማንኛውም ሁኔታ ከሶስት ቀናት መብለጥ የለበትም፡፡

22.4 አደጋ የደረሰበት ሠራተኛ በኢንሹራንስ ክሌይም ምክንያት ሳይጉላላ በአፋጣኝ ተገቢውን ህክምና እንዲያገኝ ይደርጋል፡፡ የኢንሹራንስ ክሌይም በድርጅቱ አማካኝነት ይላክለታል፡፡

22.5 በስራ ላይ አደጋ የደረሰበት ሠራተኛ የካሳ ክፍያ ከገቢ ግብር ነፃ ነው እንዲሁም ሊተላለፍ ወይም በዕዳ ማቻቻያነት ሊያዝ አይችልም፡፡

አንቀፅ ሃያ ሶስት

የዓመት ዕረፍት ፈቃድ

23.1 አንድ ሠራተኛ የዓመት ፈቃድ ለማግኘት ያለውን መብት በማናቸውም ሁኔታ ለመተው የሚያደርገው ስምምነት ውድቅ ይሆናል፡፡

23.2 የአንድ ሠራተኛን የዓመት ፈቃድ ገንዘብ መክፈል የተከለከለ ነው፡፡

23.3 አንድ ሠራተኛ በዚህ አንቀጽ መሠረት ሳይከፋፈል የሚሰጥ የዓመት ፈቃድ ከክፍያ ጋር ያገኛል፡፡ የፈቃዱ ጊዜ በምንም ሁኔታ ከዚህ በታች ከተመለከተው ማነስ የለበትም:-

ሀ) ለመጀመሪያ የአንድ ዓመት አገልግሎት አስራ ስድስት (16) የሥራ ቀናት፤

ለ) ለአሠሪው ከአንድ ዓመት በላይ ለተበረከተ አገልግሎት ለእያንዳንዱ ሁለት የአገልግሎት ዓመታት አንድ የሥራ ቀን እየተጨመረ ይሰጣል፡፡

23.4 በዓመት ፈቃድ ላይ የሚገኝ ሠራተኛ የሚከፈለው ደመወዝ ሥራ ላይ ቢሆን ኖሮ ሊከፈለው ከሚገባው ጋር እኩል ይሆናል፡፡

23.5 ለዓመት ፈቃድ ብቁ የሚያደርገውን የአገልግሎት ጊዜ ለመወሰን ሲባል በድርጅቱ ለ26 ቀናት የሠራ ሠራተኛ ለአንድ ወር እንደሰራ ይቆጠራል፡፡

23.6 የሥራ ውሉ የተቋረጠ ሠራተኛ ያልወሰደው የዓመት ፈቃድ ታስቦ በገንዘብ ይከፈለዋል፡፡

23.7 አንድ ሠራተኛ ያገለገለበት ጊዜ ከአንድ ዓመት በታች ከሆነ በአገልግሎት ዘመኑ ልክ ተመጣጣኝ የሆነ ዕረፍት በዚያው በአገለገለበት ዓመት ይሰጠዋል፡፡

23.8 ሠራተኛው የዓመት ፈቃድ ተከፋፍሎ እንዲሰጠው ሲጠይቅና አሠሪውም ሲስማማ ለሁለት ተከፍሎ ሊሰጠው ይችላል፡፡

23.9 የዓመት ፈቃድ ሠራተኛው ሲጠይቅና አሠሪውም ሲስማማ ሊተላለፍ ይችላል፡፡

23.10 አሠሪው የሥራ ሁኔታ ሲያስገድደው የሠራተኛውን የፈቃድ ጊዜ ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡

23.11 በዚህ አንቀጽ ንዑስ ተ.ቁ 23.10 እና 23.11 መሠረት የተላለፈው የዓመት ፈቃድ ከሚቀጥለው ሁለት ዓመት በላይ ሊራዘም አይችልም፡፡

23.12 አንድ ሠራተኛ በዓመት ፈቃድ እያለ ቢታመምና በህክምና ተቋም እንዲተኛ ለተደረገበት ጊዜ ብቻ የዓመት ፈቃዱ ተቋርጦ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 በአንቀጽ 85 እና 86 መሠረት የህመም ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡

23.13 በአንድ ጊዜ በተከታታይ 26 የስራ ቀናት የዓመት ዕረፍት የሚወጣ ሠራተኛ ዓመት ዕረፍት ጊዜውን ጨምሮ የሰራበትን ደመወዝ ዕረፍት ከመውጣቱ በፊት ይከፈለዋል፡፡ነገር ግን ድንገተኛ(ከአቅም በላይ) የሆነ ችግር ድርጅቱ ካጋጠመውና ከፕሮግራም ውጭ የዓመት ዕረፍት ለሚወጡ ሠራተኞች ክፍያ በመደበኛ የደመወዝ ክፍያ ሰአት የሚከፈል ይሆናል፡፡

23.14 ማንኛውም የዓመት ዕረፍት ሳይተላለፍ ወይም ሳይከፋፈል በድርጅቱ የስራ ፕሮግራም መሰረት በዓመት ውስጥ ለሰራውና ለሠራተኛው ምቹ በሆነ ጊዜ ይሰጣል፡፡

23.15 ዓመት ዕረፍት ፈቃድ ሊቋረጥ ወይም ሊተላለፍ ወይም ሊከፋፈል የሚችለው በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀፅ 79 መሰረት ነው፡፡ ነገር ግን ሠራተኛውና ድርጅቱ ከተስማሙ ዕረፍቱን ከፕሮግራም ውጭ ለመውሰድ ይቻላል፡፡

23.16 ሠራተኛው ከፕሮግራም ውጭ የዓመት ዕረፍት ፈቃድ ለመውሰድ የሚያስገድደው ችግር ሲያጋጥመው በፅሁፍ ሲጠይቅ በስራ ክፍሉ ያለው የስራ ሁኔታና የሰው ኃይል ታይቶ ዕረፍቱ ሊሰጠው ይችላል፡፡

23.17 የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ ሠራተኛ የስራ ውሉ በሚቋረጥበት ጊዜ ያልተጠቀመበት የዓመት ዕረፍት በገንዘብ ተቀይሮ ይከፈለዋል፡፡

23.18 የዓመት ዕረፍት ፈቃድ መከፋፈልን በተመለከተ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 በአንቀፅ 79.1 መሰረት እንደተጠበቀ ሆኖ ሰራተኛው የዓመት ዕረፍቱን ለቅርብ የስራ ኃላፊው አሳውቆ ከሁለት ጊዜ በላይ በማንኛውም ጊዜ እየከፋፈለ መውሰድ ይችላል፡፡

23.19 አንድ ሠራተኛ ተገቢውን የዓመት ዕረፍት ፈቃድ ወስዶ በዕረፍት ላይ እንዳለ ቢታመምና በህክምና ተቋም እንዲተኛ ለተደረገበት ጊዜ ብቻ የህክምና ፈቃድ ቢሰጠው ወይም ሴት ሰራተኛ በዓመት እረፍት ላይ እያለች ብትወልድ በፈቃዷ መጠን የዓመት ዕረፍት ፈቃዷ ይቋረጥና የወሊድ ፈቃዱ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ሆኖም የወሊድ ፈቃዱ ተቀባይነት የሚኖረው ድርጅቱ ውል ከገባበት የህክምና ተቋም ወይም በመንግስት የህክምና ተቋሞች የተሰጠ ሲሆን እና ማስረጃው በወቅቱ የቀረበ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡

23.20 አንድ ሠራተኛ በዓመት ዕረፍት ፈቃድ ላይ እያለ ህጋዊ ጋብቻ ቢፈፅም ፣ ሀዘን ቢያጋጥመው በሚያቀርበው ህጋዊ ማስረጃ መሰረት በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 ወይም በዚህ ህብረት ስምምነት ለጋብቻ እና ለሀዘን የተፈቀደ ቀን ልክ ብቻ የዓመት ዕረፍት ፈቃዱ መጠን ይራዘማል፡፡

23.21 አንድ ሰራተኛ በፈቃድ ላይ እያለ አሠሪው ለሥራ ከጠራው በመጠራቱ ምክንያት ለሚወጣው የውሎ አበልና የትራንስፖርት ወጭ ድርጅቱ ይሸፍናል፡፡ ሆኖም የዓመት ዕረፍቱን አስቀድሞ ከደመወዝ ጋር የወሰደ ሠራተኛ ተጨማሪ ደመወዝ ክፍያ አይታሰብለትም፡፡

23.22 በዓመት ዕረፍት ፈቃድ ላይ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ፈቃድ ሊራዘም አይችልም፡፡

አንቀጽ ሃያ አራት

የህመም ፈቃድ

24.1 በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 እና በዚህ ህብረት ስምምነት መሰረት የሙከራ ጊዜውን የጨረሰ ማንኛውም ሠራተኛ ከሥራ ጋር ግንኙነት የሌለው ህመም ቢደርስበት የህመም ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡ በህመም ፈቃድ ላይ እያለ የሚከፈል ደመወዝ አፈፃፀም በተመለከተ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 አንቀፅ 86 መሰረት ይሆናል፡፡

24.2 ማንኛውም የህመም ፈቃድ ድርጅቱ ውል ከገባበት የህክምና ተቋም በሚቀርበው ህጋዊ ማስረጃ መሰረት ይፈፀማል፡፡

24.3 ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ሠራተኛ በህመም ምክንያት ሥራ ሲቀር እንዲሁም የህመም ፈቃድ የተሰጠው ከሆነ ለድርጅቱ ስለ ሁኔታው እጅግ ቢዘገይ እስከማግስቱ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡

አንቀጽ ሃያ አምስት

የጋብቻ ፈቃድ

25.1 የድርጅቱ ሠራተኛ ህጋዊ ጋብቻ ሲፈፀም በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ በቁጥር 1156/2011 መሰረት ደመወዝ የሚከፈልበት ሶስት የሥራ ቀናት ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡

25.2 ሠራተኛው የጋብቻ ፈቃድ ሲፈለግ ከሰባት ቀን በፊት ለሚሰራበት የስራ ክፍል አስቀድሞ በፅሁፍ ማሳወቅ አለበት፡፡

25.3 ሠራተኛው የጋብቻ ፈቃዱን ጨርሶ ወደስራ ሲመለስ ከሚኖርበት አካባቢ ወይም ህጋዊ ስልጣን ከተሰጣቸው አካሎች ማለትም ከወሳኝ ኩነት ፣ ከሀይማኖታዊ ተቋማት እና ከመንግስት አካላት ከአንዱ ህጋዊ ማስረጃ ማቅረብ አለበት፡፡

አንቀጽ ሃያ ስድስት

የወሊድ ፈቃድ

26.1 ነፍሰ ጡር የሆነች ሠራተኛ ከእርግዝና ጋር የተያያዘ ምርመራ ለማድረግ ከደመወዝ ጋር ፈቃድ ይሰጣታል፡፡ ሆኖም ሠራተኛዋ ከምርመራው በኋላ ከሀኪም ማስረጃ ማቅረብ አለባት፡፡

26.2 ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ ከመውለዷ በፊት ሀኪም እንድታርፍ ካዘዘ ከክፍያ ጋር ዕረፍት ይሰጣል፡፡

26.3 ነፍጡር የሆነች ሠራተኛ እወልዳለሁ ብላ ከገመተችው ቀን በፊት የ30 ቀን ተከታታይ የቅድመ ወሊድ ፈቃድ እንዲሁም ስትወልድ ከወለደችበት ቀን ጀምሮ 90 ተከታታይ ቀናት የድህረ ወሊድ ፈቃድ ከክፍያ ጋር ይሰጣታል፡፡

26.4 ሠራተኛዋ ከመውለዷ በፊት የወሰደችው 30 ቀን ፈቃድ ቢያልቅ እና ካልወለደች እስከምትወልድበት ቀን ድረስ በዚህ አንቀጽ ተራ ቁጥር 26.2 መሰረት ዕረፍት ይሰጣታል፡፡ የ30 ቀን ፈቃዷ ሳያልቅ ከወለደች በዚህ አንቀጽ ተራ ቁጥር 26.3 መሰረት የምትወስደው የድህረ ወሊድ ፈቃድ ይጀምራል፡፡

26.5 ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ የወሊድ ፈቃዷን ስትጀምር የዕረፍት ጊዜ ደመወዝ በየወሩ ይከፈላታል፡፡

26.6 ለነፍጡር ሠራተኛ ከምሽት 4፡00 ሰአት እስከ ንጋቱ 12፡00 ሰአት ሥራ መስጠትና ትርፍ ሰዓት ማሰራት የተከለከለ ነው፡፡

26.7 ነፍሰጡር የሆነች የድርጅቱ ሠራተኛ በእርግዝና ምክንያት የምትሰራው ሥራ ለጊዜው እንዲቃለል ወይም እንዲለወጥ ሀኪም ሲያዝ ለጤንነቷ ተስማሚ የሆነ ሌላ ቀላል ሥራ ይሰጣታል፡፡

26.8 የፀነሰች የድርጅቱ ሠራተኛ ፅንሱ ችግር ገጥሟት ያስወረደች መሆኑ በሀኪም ሲረጋገጥ እና ሀኪሙ የህመም ፈቃድ ሲሰጣት እንደማንኛውም ህመም ደመወዝ የሚከፈልበት የህመም ፈቃድ ይሰጣታል፡፡

26.9 የፀነሰች የድርጅቱ ሠራተኛ ፅንሱ ከሰባት ወር በላይ መሆኑ ከተረጋገጠ እና የፅንስ ውርጃ ካጋጠማት የህክምና ፈቃድ ይሰጣታል፡፡

26.10 የድርጅቱ ሴት ሠራተኞች ጽንስ መያዛቸውን ወይም መፀነሳቸውን እንዳወቁ ለድርጅቱ ሰው ኃብት አስተዳደር ዋና ክፍል አራተኛ ወራቸው ጀምሮ አስቀድመው ማሳወቅና ማስመዝገብ አለባቸው፡፡

26.11 በዚህ ህብረት ስምምነት ውስጥ ያልተጠቀሱና ከህክምና ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች ፣ የገንዘብ ክፍያዎችና ሌሎች ጥቅሞች ቢኖር በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ 1156/2011 መሰረትና አግባብ ባለው ህግ ይፈፀማል፡፡

26.12 አንድ ሠራተኛ ህጋዊ ሚስቱ በወለደች ጊዜ ደመወዝ የሚከፈልበት የ3 ቀን የአባትነት ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡ በባለቤቱ ወሊድ ምክንያት ችግር ቢገጥመው ችግሩን ለመፍታት ካለው አመት ፈቃድ ወይም ነፃ ፍቃድ በመውሰድ መስተናገድ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሠራተኛው በዓመት ዕረፍት ፣ በሳምንት ዕረፍት ፣ በህመም ዕረፍትና በሀዘን ፈቃድ ላይ ከሆነ ግን ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ ሠራተኛው የአባትነት ፈቃድ የሚያገኘው ባለቤቱ ከወለደችበት ህክምና ተቋም ህጋዊ መረጃ ለድርጅቱ ሲያቀርብ ነው፡፡

26.13 ሠራተኛዋ ከወለደችና ልጇን ክትባት የምታስከትብበት ጊዜ ፈቃድ በድርጅቱ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ፈቃዷ የሚሰጣት ከጤና ተቋም መረጃ ስታቀርብ ነው፡፡

አንቀጽ ሃያ ሰባት

የሀዘን ፈቃድ

27.1 የድርጅቱ ሠራተኛ የትዳር ጓደኛ ፣ ወላጅ ፣ ተወላጅ ፣ ወንድም ፣ እህት ወይም አጎት ፣ አክስት ፣ አያት የሆነ የስጋ ወይም የጋብቻ ዘመድ ሲሞትበት ከክፍያ ጋር የሶስት ተከታታይ የስራ ቀናት ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡ ሆኖም ሠራተኛው በዚህ አንቀጽና ተ.ቁ የተጠቀሱ የቤተሰብ አባላት ሀዘን ያጋጠመው መሆኑን የሚገልጽ ህጋዊ ማስረጃ ከሚመለከታቸው አካላት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

27.2 ሠራተኛው በዚህ አንቀጽ ተ.ቁ 27.1 የተጠቀሱ የቤተሰብ አባላት ዝርዝር አስቀድሞ በሰው ኃብት አስተዳደር ቀርቦ በግል ማህደሩ እንዲመዘገቡላት ማድረግ ይኖርበታል፡፡

አንቀጽ ሃያ ስምንት

ልዩና አሳሳቢ ሁኔታ ሲያጋጥም የሚሰጥ ፈቃድ

28.1 ማንኛውም ሠራተኛ ልዩና አሳሳቢ ችግር ሲያጋጥመው ደመወዝ የማይከፈልበት እስከ ሰባት የስራ ቀናቶች የሚደርስ ነጻ ፈቃድ ሠራተኛው በሚሰራበት የስራ ክፍል እና በሰው ኃብት አስተዳደር በኩል ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን ያጋጠመው ችግር በተሰጠው ቀናት ውስጥ ካልተቀረፈለት እና ተጨማሪ ፈቃድ ካስፈለገው ለዋና ስራ አስኪያጅ አቅርቦ ሲፈቀድ ተጨማሪ ደመወዝ የማይከፈልበት ነጻ ፈቃድ ሊሰጠው ይችላል፡፡

አንቀጽ ሃያ ዘጠኝ

ለመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ሥራ የሚሰጥ ፈቃድ

29.1 የሠራተኛ ማህበር መሪዎች የስራ ክርክር ለማቅረብ ፣ የህብረት ስምምነት ለመደራደር ፣ በማህበር ስብሰባ ለመገኘት ፣ በሴሚናሮችና በስልጠና ለመካፈል እንዲችሉ ከክፍያ ጋር ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ ሆኖም ሠራተኛ ማህበሩ ከሚመለከተው አካል አስቀድሞ ለድርጅቱ ደብዳቤ ማቅረብና ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡

29.2 የሠራተኛ ማህበር ስራ አስፈጻሚ አካላት በተለያዩ ድርጅቶች የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ሲያስፈልግ በቅድሚያ በደብዳቤ ለድርጅቱ ማሳወቅና ማስፈቀድ እንዳለበት ሆኖ በአንድ ዓመት ውስጥ ለአንድ ጊዜ ብቻ ከሶስት ላልበለጡ ስራ አስፈጻሚዎች ከአምስት ቀናት ያልበለጠ ፈቃድ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ ሆኖም ልምድ ልውውጥ ከወሰዱበት ተቋም ልምድ ልውውጡን የወሰዱ መሆናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

29.3 ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በወር አንድ ቀን ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የስራ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ሠራተኛ ማህበሩ በጽሁፍ ለድርጅቱ ሲጠይቅና አሳማኝ ሆኖ ሲገኝ ሊሰጥ ይችላል፡፡

29.4 ለሠራተኛ ማህበር ሊቀመንበር ደመወዝ በሳምንት ለሁለት ጊዜ ሰኞ እና ሐሙስ ደመወዝ የሚከፈልበት የግማሽ ቀን ፈቃድ ይሰጣል፡፡

29.5 በየስራ ክፍሉ ለሚገኙ የሠራተኛ ማህበሩ የምክር ቤት አባላት ከሠራተኛ ማህበሩ ስራ አስፈጻሚ ጋር ለመወያየት ፣ የሶስት ወር ሪፖርት ለመስማት እንዲሁም እንደአስፈላጊነቱ ከእነዚህም ውጭ በሆኑ ጉዳዮች ለመወያየት ሠራተኛ ማህበሩ በጽሁፍ ሲጠይቅ ድርጅቱ ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ ይሰጣል፡፡

29.6 ሠራተኛው ለፌደሬሽን እና ኮንፌደሬሽን ምክር ቤት ተመራጭ ሲሆን እና ለድርጅቱ ከሚመለከተው አካል በጽሁፍ ሲደርሰው እና ከፌደሬሽኑ ወይም ከኮንፌደሬሽኑ ደመወዝ የማይከፈለው መሆኑ በጽሁፍ ሲረጋገጥ ድርጅቱ ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡ ተመራጮቹም የስራ ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁ ወደመደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ ያደርጋል፡፡

29.7 ሆኖም በዚህ አንቀጽ ተ.ቁ 29.6 መሰረት የፌደሬሽንና ኮንፌደሬሽን ምክር ቤት አባልነት ስራቸውን አጠናቀው ወደድርጅቱ የሚመለሱ ሠራተኞች ቀደም ሲል ይሰሩበት የነበረው የስራ መደብ ላይ ሌላ ሰው ተተክቶ ከሆነ ቀደም ሲል ይዘው ከነበረ የስራ መደብ ጋር ተቀራራቢ የሆነ የስራ መደብ ላይ ይመደባሉ፡፡

አንቀጽ ሰላሳ

ልዩ ልዩ ፈቃዶች

30.1 ድርጅቱ ለማንኛውም ሠራተኛ ከፖሊስ ፣ ከፍርድ ቤት ወይም ህጋዊ ሥልጣን ባለው አካል ለምስክርነት ወይም ለአስረጅነት መምሪያ ሲደርሰው በቅድሚያ ለድርጅቱ በማሳወቅና በዚህ ለመቅረቱ መረጃ ሲያቀርብ ፣ የሲቪል መብቱም ለመጠየቅና የሲቪል ግዴታዎችን ለመፈፀም እንዲሁም ለሥራ ክርክር ጉዳይ ከሥራ ሲለይ ፈቃድ ከደመወዝ ጋር ይሰጠዋል፡፡ ማስረጃ ማቅረብ ግን ይኖርበታል፡፡

30.2 አንድ ሠራተኛ ከድርጅቱ ጋር የሥራ ክርክር ሲመሰረት ፈቃድ ከደመወዝ ጋር ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን ከሚመለከተው አካል ማስረጃ ማምጣት ይኖርበታል፡፡

30.3 በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙ ሾፌሮች ለተቀጠሩበት የመንጃ ፈቃድ ዓይነት ለማሳደስ እና በሚሰጠው ፈተና ለመሳተፍ ፈቃድ ሲጠይቁ ከደመወዝ ጋር ይሰጣቸዋል፡፡ ፈተና የተሰጠው ለመሆኑ ማስረጃ ማምጣት ይኖርባቸዋል፡፡

30.4 ማንኛውም ሠራተኛ ድርጅቱ በሚያዘጋጀው ወይም በድርጅቱ አማካኝነት በሚካሄደው የሥልጠና ፕሮግራም ሲሳተፉ ወይም ድርጅቱ አምኖበት በሀገር ውስጥና ውጭ ሀገር በሚሰጥ ሥልጠናና ሴሚናር ሲልከው ፈቃድ ከደመወዝ ጋር ይሰጠዋል፡፡

30.5 ማንኛውም ሠራተኛ በግሉ የሚማር ከሆነ እና በቅድሚያ ለድርጅቱ አሳውቆ ፈቃድ ለተሰጠበት የትምህርት ፕሮግራም በትምህርት ቤት ፈተና የቦታው ርቀት ከግምት ውስጥ እየገባ ፈተና ለሚወስድባቸው ሰዓቶች የፈተና ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን ለብሄራዊ ፈተና ተፈታኞችና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ (COC) ፈተና ለሚወስዱ ሙሉ ቀን ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡ ሆኖም ማስረጃ ማቅረብ ግን ይኖርበታል፡፡

አንቀጽ ሰላሳ አንድ

የሥራ ልብስና የአደጋ መከላከያ መሳሪያዎች

31.1 ድርጅቱ ለሠራተኛው እንደሥራው ጸባይ የሚያስፈልጉትን የስራ ልብስና የአደጋ መከላከያ ደህንነት መሳሪያዎች በዚህ ህብረት ስምምነት በተያያዘው አባሪና የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጥናት መሰረት ይሰጣል፡፡

31.2 ለሠራተኛው የተሰጠው የደንብ ልብስና የአደጋ መከላከያ መሳሪያ በሥራ ላይ እያለ ከሠራተኛው ቁጥጥር ውጭ በሆኑ ምክንያቶች ቢበላሽ ፣ በአሲድና በመሳሰሉት ከጥቅም ውጭ ከሆነ ይህንኑ ሠራተኛው በጊዜው በክፍል ኃላፊውና ለሚመለከታቸው በማሳየት አዲስ ይሰጠዋል፡፡

31.3 የስራ ልብስና የአደጋ መከላከያ መሳሪያ በየስድስት ወሩ መስከረምና መጋቢት ወር ይሰጣል፡፡ ሆኖም በአባሪው ላይ የተጠቀሱ ስድስት ወርና ከዚያ በላይ አገልግሎት የሚሰጡ አልባሳት በአባሪው በተጠቀሰው መሰረት የሚፈጸም ይሆናል፡፡

31.4 ሠራተኛው በተሰጠው የሥራ ልብስና የአደጋ መከላከያ በተመደበበት ስራ እና በሥራ ሰዓት ሁሉ የመጠቀም ኃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡

31.5 የሥራ ልብስና የአደጋ መከላከያ መሳሪያ በማይጠቀም ሠራተኛ ላይ በዚህ ህብረት ስምምነት የሥነ-ስርዓት እርምጃ አወሳሰድ እንደተጠበቀ ሆኖ እስከሥራ ስንብት እርምጃ ይወሰዳል፡፡ መሰረታዊ ሠራተኛ ማህበሩም ሠራተኞች የሥራ ልብሱን እንዲለብሱና የአደጋ መከላከያ አልባሳት እንዲጠቀሙ እገዛ ያደርጋል፡፡

31.6 የሥራ ጸባያቸው ሳሙና የሚያስፈልጋቸው ሠራተኞች ድርጅቱ ከ300 ግራም ያላነሳ ሳሙና ወይም አጃክስ ይሰጣል፡፡ ቀደም ሲል ለሠራተኛ ይሰጥ የነበረው ሳሙና እንደተጠበቀ ሆኖ የሥራ ፀባያቸው ሳሙና ለሚያስፈልጋቸው ሠራተኞች የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በሚሰጠው አስተያየት መሰረት በድርጅቱና በሠራተኛ ማህበሩ በጋራ ይወሰናል፡፡

31.7 የሥራ ፀባያቸው ወተት የሚያስፈልጋቸው እንደህትመት ፣ ሪሳይክል የመሳሰሉ የስራ ክፍሎች የወተት አበል በየወሩ ከደመወዝ ጋር እየተካተተ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ሆኖም ሌሎች የስራ ክፍሎች የስራ ጸባያቸው ወተት የሚያስፈልገው ሆኖ ሲገኝና በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በሚሰጥ አስተያየት እንዲሁም ድርጅቱና ሠራተኛ ማህበሩ በጋራ በሚያደርጉት ጥናት መሰረት ታይቶ የሚፈጸም ይሆናል፡፡

አንቀጽ ሰላሳ ሁለት

የቀብር ሥነ-ስርዓት

32.1 አንድ ሠራተኛ በስራ ላይ አደጋ ቢሞት ለተሸከርካሪ አመቺ በሆነ መንገድ ድርጅቱ የአስክሬን ማጓጓዣ ተሸከርካሪ የሚያቀርብ ወይም የትራንስፖርት ወጪ የሚሸፍን ይሆናል፡፡ ከስራ ላይ አደጋ ውጭ ለሚያጋጥሙ ህመሞች ምክንያት ለሚመጣ ሞት ግን ድርጅቱ እንደሁኔታው እያየ ለአስከሬን ማጓጓዣ ትራንስፖርት ወይም የትራንስፖርት ወጪ የሚሸፈንበት ሁኔታ ሊያመቻች ይችላል፡፡

32.2 የስራ ላይ አደጋ ደርሶበት የሞተ ሠራተኛ የቀብር ስነ ስርአት ወጪ የሚሆን የሶስት ወር ደመወዝ ወይም ከብር 6000.00 (ስድስት ሽህ ብር) ያልበለጠ ለቤተሰቡ ክፍያ ይፈጸማል፡፡ ከስራ ላይ አደጋ ውጭ ለሆኑ የቀብር ስነ ስርአት ወጪና ሌሎች ማቋቋሚያዎችን ድርጅቱ እንደሁኔታው እያየ ለቤተሰቡ ድጋፍ ሊያደርግ ይችላል፡፡

32.3 የድርጅቱ የስራ ባልደረባ ሲሞት በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙ የሠራተኛው የቅርብ የስራ ባልደረቦች እና የሠራተኛ ማህበር ተወካይ ጨምሮ በቀብር ስነ ስርአቱ ላይ እንዲገኙ ፈቃድ ይሰጣል፡፡ ሆኖም የቀብር ስነ ስርአቱ ከድርጅቱ የስራ ክልል ውጭ የሚፈጸም ከሆነ ለሁለት ሠራተኞች እና ለአንድ የሠራተኛ ማህበር ተወካይ ከደርሶ መልስ ውጭ የአንድ ቀን ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ ይሰጣል፡፡

32.4 የድርጅቱ የስራ ባልደረባ በህይወት ሲለይ ወይም ሲሞት ለቀብር ስነ ስርአት ማስፈጸሚያ ብር 3000.00 (ሶስት ሽህ ብር) ለሟች ቅርብ ቤተሰብ ይሰጣል፡፡

አንቀጽ ሰላሳ ሶስት

ለሠራተኞች የሚሰጥ የብድር አገልግሎት

33.1 ሠራተኛው ከአቅም በላይ የሆነ ችግር በህመም ወይም በተለያዩ ቤተሰባዊ ጉዳዮች ሲያጋጥመው እና ስራውን ተረጋግቶ ለመስራት በሚቸገርበት ሁኔታ ላይ ሲገኝ ከዚህ በታች በተጠቀሰው አሰራር መሰረት ከወለድ ነጻ የሆነ ብድር ይሰጠዋል፡፡

1. ሠራተኛው ያጋጠመው ችግር አሳማኝ ሲሆን የድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ከዋና ስራ አስኪያጅ ጋር በመመካከር ብድሩን ሲፈቅዱ የሁለት ወር ደመወዝ በአስራ ሁለት ተከታታይ ወራት ተከፍሎ በሚያልቅ በብድር ሊሰጠው ይችላል፡፡ ሆኖም ብድር ጠያቂው ከውስጥ ሠራተኞች ሁለት ቋሚ ሠራተኞችን በዋስት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

2. ሠራተኛው ያቀረበው የብድር ጥያቄ የአንድ ወር ደመወዝ ከሆነ በሶስት ወራት ፣ በቀጣይ ወር ካለው ደመወዝ የሚቆረጥ ቅድመ ክፍያ (አድቫንስ) ከሆነ የወር ደመወዙ 1/3ኛ ድረስ በድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይም በተወካዩ በኩል ከማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋር በመወያየት ሲፈቀድ የሚፈጸም ይሆናል፡፡

3. ከላይ የተጠቀሱትን የብድር ጥያቄዎች ማስተናገድ የሚቻለው በድርጅቱ ውስጥ ተቀጥሮ የሙከራ ጊዜውን ላጠናቀቀ ቋሚ ሠራተኛ ብቻ ነው፡፡ የብድር ጥያቄ ማመልከቻ ፣ የተፈቀደለት መሆኑን የሚገልጽ ሰነድ እና የዋስ ማስረጃ ከብድር ጠያቂ ግል ማህደር ላይ የሚታሰር እና ኮፒው ለፋይናንስ በደብዳቤ የሚተላለፍ ይሆናል፡፡

4. በዚህ አንቀጽ በተ.ቁ 2 እና 3 የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ የሠራተኛው ችግር አሳሳቢ በሚሆንበት እና ለማኔጂንግ ዳይሬክተር ቀርቦ ሲፈቀድ የብድር መጠንና የመክፈያ ጊዜው እንደሁኔታው እየታየ የማሳደግና የማራዘም ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል፡፡

5. ሠራተኞችን ከማበረታታትና ለረዥም ጊዜ እንዲቆዩ ከማድረግ አግባብ ከተለያዩ ድርጅቶች የቤት ቁሳቁሶችን ለመግዛት የሚያስችል በረዥም ጊዜ ብድር ለመውሰድ ስምምነት ላይ ሲደርስ ድርጅቱ ዋስትና በመግባት ከወርሃዊ ደመወዙ ላይ ተቀናሽ እና ዕቃው ለተወሰደበት ድርጅት ገቢ በማድረግ ሠራተኛው ተጠቃሚ የሚሆንበት አሰራር ሊያመቻች ይችላል፡፡

አንቀጽ ሰላሳ አራት

የካፍቴርያ አገልግሎት

34.1 ድርጅቱ ለሰራተኛው አገልግሎት የሚሰጥ ካፍቴሪያ የድርጅቱን አቅም በፈቀደ መሰረት ያዘጋጃል፡፡

34.2 ዓመታዊ ጠቅላላ ዕድሳትና ለካፍቴሪያ አገልግሎት የሚውል ውሀና መብራት ድርጅቱ ይችላል፡፡

34.3 ድርጅቱ ለሠራተኛ የተዘጋጀው ካፍቴርያ ውስጥ የሚገኙትን ንብረቶች ፣ የምግብ ጥራት ፣ የምግብ አሰራር እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸውን ማንኛውም የካፍቴሪያ እንቅስቃሴና አፈፃፀም ይቆጣጠራል፡፡

34.4 ማንኛውም ሠራተኛ የካፍቴሪያውን ንብረቶች እንደግል ንብረቱ መንከባከብና በአግባቡ የመጠቀም ግዴታ አለበት፡፡

34.5 የካፍቴሪያው አገልግሎት የምግብ ተመን የድርጅቱን ሠራተኛ የመክፈል አቅም መነሻ በማድረግ በወቅቱ ያለውን የገበያ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የሠራተኛ ማህበሩን ያካተተ ኮሚቴ በሚያቀርበው ጥናት መሰረት የሚወሰን ይሆናል፡፡

34.6 የጤና ምርመራ ተደርጎላቸው ከተላላፊ ህመም ነጻ ያልሆኑ ሠራተኞች በካፍቴሪያው እንዲሰሩ አይፈቀድም፡፡ ሠራተኞቹ ከተላላፊ ህመም ነፃ መሆናቸውን እና የህክምና ማስረጃ ማቅረብ ኃላፊነት በወቅቱ ካፍቴሪያውን ተከራይቶ እየሰራ የሚገኘው የካፍቴሪያው ባለቤት ይሆናል፡፡

አንቀጽ ሰላሳ አምስት

ስፖርት

35.1 ሠራተኛው በስፖርት አካሉንና አዕምሮውን ለማጎልበትና ጤናማ ዜጋ ለመሆን ያስችለው ዘንድ ድርጅቱና ሠራተኛ ማህበሩ አቅም በፈቀደ መልኩ የማቴርያል ፣ የሞራልና አስፈላጊውን የሆኑ ግብአቶችን በመደገፍ ይተባበራሉ፡፡

አንቀጽ ሰላሳ ስድስት

የሥነ-ስርዓት እርምጃ

36.1 የስነ ስርአት እርምጃ አወሳሰድ አፈጻጸም

1. ማንኛውም ሠራተኛ ጥፋት መፈፀሙን የቅርብ ስራ ኃላፊ እንደተረዳ በአጥፊው ሠራተኛ ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወሰድ ጥፋቱን በክስ ማቅረቢያ ቅጽ ላይ ዘርዝሮ እና ሠራተኛው እንዲያውቀውና እንዲፈርምበት በማድረግ በ24 ሰአት ውስጥ ቀጥሎ ለሚገኘው የስራ ኃላፊ ወይም የስራ ክፍል መድረስ ይኖርበታል፡፡

2. ሠራተኛው የፈጸመው የድስፕሊን ግድፈት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና ከዚያ በታች የሆነ ቅጣት የሚያስቀጣው ከሆነ በቅርብ ስራ ኃላፊው በኩል ውሳኔ እንዲሰጥበት ይደረጋል፡፡ ሠራተኛው የፈጸመው ጥፋት በቅርብ ስራ ኃላፊው በኩል ውሳኔ የማይሰጥ ከሆነ የክስ ቻርጁ ተሞልቶ ሠራተኛውና የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ፈርመውበት ወደ ሰው ኃብት ልማትና አስተዳር መምሪያ ተልኮ በህብረት ስምምነት ላይ ባለው የቅጣት ዝርዝር መሰረት ተፈጻሚነት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡ ጉዳዩ ውስብስብና ማጣራት የሚያስፈልገው ጉዳይ ከሆነ በዲስፕሊን ኮሚቴ በኩል ታይቶ ውሳኔ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡

3. አንድ የተሟላ የሠራተኛ ጥፋት መግለጫና የቅጣት ውሳኔ ማሳወቂያ ቅጽ ጥፋቱ እንደተፈፀመ ወይም አጥፊው እንደታወቀ አስፈላጊ ሁሉ ተፈፅሞ የቅጣት ውሳኔው ሠራተኛው በሚሰራበት መምሪያ እና በሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር መምሪያ በኩል የሚሰጥ ከሆነ በሦስት ቀናት ውስጥ ፣ ጥፋቱ ተጨማሪ ማጣራት የሚያስፈልገው ከሆነና በዲስፕሊን ኮሚቴ የሚታይ ከሆነ ደግሞ በ15 (አስራ አምስት) ቀናት ውስጥ ለሠራተኛው እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡ ነገር ግን በተጠቀሱ ቀናቶች ውስጥ የቅጣት እርምጃው ካልተወሰደ ቅጣቱ እንደተተወ የሚቆጠርና ተፈጻሚነት የማይኖረው ይሆናል፡፡

4. በዚህ ህብረት ስምምነት መሰረት የሚወሰዱ የስነ-ሥርዓት እርምጃዎች በፍርድ ቤትና በሌላ ተቋሞች ከሚወሰዱ እርምጃዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የላቸውም፡፡

5. እርምጃ የተወሰደበት ሠራተኛ የደብዳቤው ግልባጭ ሠራተኛ ማህበሩ እንዲያውቀው ወይም እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡ በተወሰደው እርምጃ ሠራተኛው ቅሬታ ካለው ሠራተኛ ማህበሩና የሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር መምሪያ ቅሬታውን በጋራ ለመፍታት ጥረት ያደርጋሉ፡፡

6. ሠራተኛው ምንም ጥፋት ሳይኖረው እርምጃ እንዲወሰድበት ያደረገ ኃላፊ ላቀረበው ክስ በህብረት ስምምነቱ ወይም በሥራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡

36.2 የዲሲፕሊን ጥፋቶችና የቅጣት አወሳሰን

36.2.1 የዲሲፕሊን ጥፋቶችና የቅጣት አወሳሰን ሂደት

1. በማንኛውም ሠራተኛ ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ የሚወሰደው ሠራተኛውን ከጥፋቱ ለማረም ፣ ሥራ እንዳይበደል ለመቆጣጠርና ሌሎች ሠራተኞች እርምጃ ከተወሰደበት ሠራተኛ ትምህርት በመውሰድ ከጥፋት እንዲቆጠቡ እና ስራቸውን በአግባቡ እንዲከውኑ ለማድረግ ነው፡፡

2. የዲሲፕሊን እርምጃ ከመወሰዱ በፊት የጥፋቱ ክብደትና ሠራተኛው በፊት የነበረው ጸባይ ፣ መልካም አገልግሎትና ለጥፋቱ መንስኤ በሆኑት ሁኔታዎች በጥንቃቄ መመርመር ይኖርባቸዋል፡፡

3. የዲሲፕሊን ቅጣት የሚወሰድባቸው የቅጣት ዓይነቶች ከዚህ ህብረት ስምምነት ጋር በተያያዘው አባሪ መሰረት የቅጣት ደረጃውን ጠብቀው ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡

4. በዚህ ህብረት ስምምነት ከተጠቀሱት የስር ስርአት እርምጃ ቅጣት ሠንጠረዥ አባሪ ውስጥ ያልተጠቀሱ ጥፋቶች ሲፈጸሙ የጥፋቱ ክብደት እየተመዘነ በአባሪው ከተዘረዘረው ውስጥ በተመሳሳይ ወይም በተቀራረበ አንቀጽ እርምጃ ይወሰዳል፡፡

5. በአንድ ጊዜ ሁለት ጥፋቶች የፈፀመ ሠራተኛ በሁለቱም ጥፋቶች ለደረሰው ጉድለት ተጠያቂ ሆኖ ከሁለት በአንዱ ከፍተኛ ለሠራው ጥፋት በሚያስቀጣው አንቀጽ ብቻ ይቀጣል፡፡

36.2.2 ከሥራና ከደመወዝ ስለማገድ

1. አንድ የድርጅቱ ሠራተኛ ከሥራ ታግዶ የሚቆይበት ምክንያት፡-

ሀ. ከተከሰሰበት ጉዳይ ጋር አግባብ ያላቸውን ማስረጃዎች በማበላሸት ወይም በመደበቅ ምርመራውን የሚያሰናክል ሆኖ ሲገመት፣

ለ. በድርጅቱ ንብረትና በህይወት ላይ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ ሲጠረጠር ሠራተኛውን ከአስራ አምስት ቀን ለማይበልጥ ጊዜ ከሥራና ደመወዝ አግዶ ለማቆየት ይቻላል፡፡

2. አንድ የድርጅቱ ሠራተኛ በወንጀል ወይም በዲስፕሊን ጥፋት በህግ የተከሰሰ እንደሆነና ሲመሰከርበት ጥፋቱ ከሥራው የሚያሰናብተው መሆኑ ሲገመት ድርጅቱ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ እንኪሰጥበት ድረስ ከሥራ ታግዶ እንዲቆይ ሊደረግ ይችላል፡፡

3. ድርጅቱ ተፈጸመ የተባለውን ጥፋት መርምሮ በ15 (አስራ አምስት) የሥራ ቀናት ውስጥ ለሠራተኛው እና ለሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ውሳኔውን ያሳውቃል፡፡

4. ሠራተኛው ጥፋት ያልፈፀመ መሆኑ ሲረጋገጥ የታገደበት ጊዜ ደመወዝ ተከፍሎት ወደ ስራው ይመለሳል፡፡

36.3 የዲሲፕሊን ኮሚቴ

36.3.1 የዲስፕሊን ኮሚቴ አወቃቀር

1. የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ውስብስብና ከፍተኛ የዲሲፕሊን ጉድለቶች ሲከሰቱ ጉዳዩን ለማጣራትና አስፈላጊውን መረጃ በመመርመር ለውሳኔ የሚያቀርብ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ሊያቋቁም ይችላል፡፡

2. የዲስፕሊን ኮሚቴ አባላት

ሀ/ የዲስፕሊን ኮሚቴ ጸሀፊውን ጨምሮ አምስት አባላት ይኖሩታል፣

ለ/ የኮሚቴው ሰብሳቢ ፣ ሁለት አባላትና ፀሐፊው በድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ይመደባሉ፣

ሐ/ ከመሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር አንድ የኮሚቴ አባል ይመረጣል፡፡

36.3.2 የዲሲፕሊን ኮሚቴ ስልጣንና ተግባር

1. የሥነ ሥርዓት እርምጃዎችን በመከተል ውስብስብ የሆኑ ከፍተኛ የዲሲፕሊን ጉድለቶችን በሚመለከት ዋና ስራ አስኪያጅ በኮሚቴው እንዲጣራ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውና ለኮሚቴው ሲመራለት ያጣራል ፣ ይመረምራል ፣ የውሳኔ ሀሳብም ያቀርባል፡፡

2. የተከሰሰው ሠራተኛ መልስ እንዲሰጥበት በደብዳቤ ይጠየቃል፡፡ ሠራተኛው መልሱን ይዞ የሚቀርብበትን ሰዓት ፣ ቀንና ቦታም ይወስናል፡፡

3. ሠራተኛው መልሱን ይዞ እንዲቀርብ በተቀጠረበት ሰዓት ፣ ቀንና ቦታ በጽሁፍ ይዞ መቅረብ አለበት፡፡ ሆኖም ሠራተኛው መልሱን በወቅቱ ካላቀረበ ኮሚቴው የቀረቡለትን ማስረጃዎች መሰረት በማድረግ ለዋና ስራ አስኪያጅ የውሳኔ ሃሳቡን ያቀርባል፡፡

4. ሠራተኛው መልሱን ይዞ ከቀረበ ከሁለቱም ወገኖች የቀረቡለትን ማስረጃዎች መርምሮ የውሳኔ ሀሳቡን ያቀርባል፡፡

5. ኮሚቴው የሠራተኛ የዲሲፕሊን ጉዳዮች ሲያጣራ አስፈላጊ የሆኑ የሰው ወይም የፅሁፍ ማስረጃዎች ከማንኛውም የስራ ክፍል እንዲቀርብለት ወይም የሚመለከታቸው ሠራተኞች ቀርበው እንዲያስረዱ ሊያዝ ይችላል፡፡

6. ጉዳዩ በዲሲፕሊን ኮሚቴ እየታየ ያለ ሠራተኛ በፅሁፍ ካቀረበው መልስ በተጨማሪ በቃል እንዲያስረዳ ሲጠይቅ ይፈቀድለታል፡፡

7. ማንኛውም የዲስፕሊን ኮሚቴ አባል የሆነ ሠራተኛ በስብሰባው ወቅት የሚካሄዱትን ሁኔታዎች በሚስጢር መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ጉዳዩ ለባለጉዳዩ ወይም ለማይመለከተው ግለሰብ ሁኔታውን በገለፀው የኮሚቴው አባል ፣ ሰብሳቢ ወይም ፀሐፊ በዲሲፕሊን ጉድለት ተጠያቂ ይሆናል፡፡

8. ማንኛውም ወደ ዲሲፕሊን ኮሚቴ የሚቀርቡ ጉዳዮች በ15 ቀናት ውስጥ ተጣርቶ እንዲጣራ ላዘዘው ኃላፊ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

9. የድርጅቱ ሠራተኛ የቀረበበትን ክስ በመካድ መልስ የሰጠ እንደሆነ አጣሪው አግባብ ያላቸውን ማስረጃዎች ከመረመረ በኋላ ለሚመለከተው ስራ ኃላፊ የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባል፡፡

10. በቀረበው መረጃና የውሳኔ ሀሳብ ላይ ተመስርቶ ዋና ስራ አስኪያጅ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል እርምት የሚያስወስድ ከሆነም በዚህ ህብረት ስምምነት ፣ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 ፣ በድርጅቱ መመሪያና ደንብ እና ተያያዥ የሆኑ አግባብነት ባላቸው ህጎች መሠረት ቅጣት ይወሰናል፡፡

36.3.3 ምልዓተ ጉባኤና የድምጽ አሰጣጥ

1. ኮሚቴው መደበኛ የስብሰባ ጊዜ አይኖረውም፡፡ ኮሚቴው እንዲሰበሰብ ሲያስፈልግ በሰብሳቢው አማካይነት ጊዜውና ቦታው ይወሰናል፡፡

2. ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ የሚያሳልፈው በድምጽ ብልጫ ይሆናል፡፡

3. ድምጽ እኩል በእኩል የተከፈለ እንደሆነ ሰብሳቢው ያለበት ወገን ያቀረበው ሃሳብ ያልፋል በሃሳብ የተለየው አባል የተለየበትን ምክንያት በግልጽ ማስፈር አለበት ወይም የልዩነት ሀሳብ ያለው አባል ልዩነቱን በቃለ ጉባዔው ውስጥ አስፍሮ ይፈርማል፡፡

36.3.4 የኮሚቴው አገልግሎት ዘመን

1. የኮሚቴው አባላት የአገልግሎት ዘመን አንድ ዓመት ይሆናል ሆኖም የአገልግሎት ዘመናቸውን የጨረሱ የኮሚቴው አባላት እንደገና ሊመደቡ ወይም ሊመረጡ ይችላሉ፡፡
2. አንድ የኮሚቴ አባል ሥራውን በመልቀቅ ወይም ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት በአባልነት ሊቀጥል ካልቻለ የኮሚቴው ሰብሳቢ ለዋና ስራ አስኪያጅ በማሳወቅ በምትኩ እንዲተካ ያደርጋል፡፡ ሆኖም የተጓደለው የኮሚቴው አባል የሠራተኛ ማህበር ተወካይ ከሆነ ሠራተኛ ማህበሩ ምትክ አባል በደብዳቤ ያሳውቃል፡፡

36.3.5 ኮሚቴው ስራውን የሚመራበት ስነ ስርዓት

36.3.5.1 ከአባልነት ስለመሰረዝና ከስብሰባ ስለመነሳት

1. ማንኛውም የዲስፕሊን ኮሚቴ አባል ክስ ከቀረበበት ሠራተኛ ጋር ፀብ ወይም የሥጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ያለው መሆኑ ሲረጋገጥ ለዚያ ጉዳይ ብቻ ከስብሰባው እንዲነሳ ተደርጎ በቀሩት አባላት ይቀጥላል፡፡ ሆኖም በዚህ አንቀጽ መሰረት ከአባልነት የሚነሳው ሰብሳቢው ወይም ሠራተኛ ማህበር ከሆነ ምትክ ይደረጋል፡፡

2. ማንኛውም የዲስፕሊን የኮሚቴ አባል፡-

ሀ/ በኮሚቴው በመታየት ላይ ያለን ጉዳይ በሚመለከት ሚስጥር ያባከነ ፣

ለ/ የኮሚቴውን ሥራ በማንኛውም አኳኋን ያደናቀፈ ከአባልነት ሊሰረዝ ይችላል፣

36.3.5.2 የዲስፕሊን የጥፋት ዓይነቶችና የሚወሰዱ የቅጣት እርምጃዎች

የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 ፣ በሒፋም/ሰኢድ አሊ ፒፒ ከረጢት ፋብሪካ እና በሠራተኛ ማህበር መካከል በተደረገ በዚህ የህብረት ስምምነት የዲስፕሊን እርምጃ አወሳሰድ እና በሰው ኃብት አስተዳደር መመሪያ የተቀመጡ የዲስፕሊን እርምጃ ዝርዝሮች በተለያየ ደረጃ ለሚፈጸሙ የስነ ስርአት ጉድለቶች የሚወሰዱ እርምጃዎችን መሰረት ይሆናል፡፡

36.4 የዲስፕሊን ቅጣት ዓይነቶችና አመዳደብ

36.4.1 ቀላል የዲስፕሊን ጥፋቶች

ሀ/ የቃል ማስጠንቀቂያ በቅርብ ኃላፊዎች የሚሰጥ ፣

ለ/ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ በሚመለከተው ኃላፊ የሚሰጥ ፣

36.4.2 ከባድ የዲስፕሊን ጥፋቶች

1. ማንኛውም ሠራተኛ ከባድ የዲስፕሊን ጥፋት የፈፀመ እንደሆነ በበቂ ማስረጃ በስራ ክፍሉ ሲረጋገጥ ሰው ኃብት ልማትና አስ/ጠቅ/አገ/መምሪያ ለዋና ስራ አስኪያጅ በማሳወቅ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፡፡

2. ማንኛውም ሠራተኛ ከባድ የዲስፕሊን ጥፋት የፈፀመ እንደሆነ ጉዳዩ በሠው ኃብት ልማት አስ/ጠቅ/አገ/መምሪያ ውሳኔ ወይም በዲሲፕሊን ኮሚቴ በበቂ ማስረጃ ተረጋግጦ ሲቀርብ በዋና ስራ አስኪያጅ ሲጸድቅ ከዋና ክፍል በታች የሆኑ የስራ መደቦችን በሰው ኃብት ልማ/አስ/ጠቅ/አገ/መምሪያ እንዲሁም ከዋና ክፍል በላይ የሆኑትን የስራ መደቦችን በዋና ስራ አስኪያጅ ከስራ ደረጃና ደመወዝ ዝቅ የማድረግ ፣ ከሥራ የማሰናበት ስልጣንና ኃላፊነት ይኖራቸዋል፡፡

36.4.3 ያለማስጠንቀቂያ የስራ ውል የሚያቋርጡ ጥፋቶች

1. የድርጅቱን ንብረት የሠረቀ ወይም ያጭበረበረ ወይም ለሥርቆት ሆን ብሎ የተባበረ ወይም ለመስረቅ ያደረገው ሙከራ በበቂና ተጨባጭ መረጃ ከተረጋገጠ፣

2. የድርጅቱን ሰነድ ያጠፋ ፣ የደለዘ ፣ ከሠራተኛ የግል ማህደር ውስጥ ማንኛውንም መረጃ ያጠፋ ወይም እነዚህን ጥፋቶች እንዲፈፅሙ ያደረገ ወይም ለሌላ አሳልፎ የሰጠ፣

3. የድርጅቱን የሰዓት መቆጣጠሪያ ፣ የደመወዝ አበል ፣ የክፍያ ሂሳብ ማስረጃ የምርት ምዘናና ምዝገባ ፣ የምርት የጥራት ደረጃ መቆጣጠሪያ ፣ የዕድገት ማወዳደሪያ ነጥቦችን ፣ የማነቃቂያ ክፍያን ሌሎች ተመሳሳይ ሥራዎችን ከትክክለኛው መንገድ ውጭ ሆን ብሎ ሌላውን ሠራተኛ ለመጥቀም የሚችል ወይም ሊጎዳ የሚችል ሥራ የሰራ ወይም የድርጅቱን ሚስጥርና መረጃ ለሌላ አሳልፎ የሰጠ፣

4. በስካር መንፈስና በአደንዛዥ ዕፅ ተመርዞ ወደ ስራ የገባ የድርጅቱን መኪና ያሽከረከረ ሹፌር፣ የምርት መሳሪያ ያንቀሳቀሰ፣ ጉዳት ያደረሰ ወይም አካባቢውን የበጠበጠ ማንኛውም ሠራተኛ ፣

5. የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ከተቀበለ በኋላ ሌላ ጥፋት የፈፀመ ፣

6. ሠራተኛው የስራ ሰአት ለማክበር የማይችልባቸው ሁኔታዎች ተብለው በዚህ ህብረት ስምምነት ፣ በስራ ደንብ ወይም በስራ ውሉ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ውጭ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው በስድስት ወር ውስጥ በጠቅላላው ለስምንት ጊዜ የስራ ሰአት አለማክበር ወይም በስድስት ወር ውስጥ ለአምስት ቀናት ያለህጋዊ ምክንያት ከስራ የቀረ ወይ በስራው ላይ ያልተገኘ ሠራተኛ ፣

7. ሀሰት መሆኑን እያወቀ ሊያገኝ የማይገባውን ጥቅም ለማግኘት ወይም ሌሎች እንዲያገኙ ለማድረግ የተሰጠውን ፈቃድ የደለዘ ወይም ከተፈቀደለት በላይ የጨመረ ወይም ፊርማ አስመስሎ የፈረመ እንዲሁም የደለዘ፣ የሌላው ሰው ሰዓት መቆጣጠሪያ የሞላ ያስመሰለና በማንኛውም የሥራ ዘርፍ ሆን ብሎ ሀሰተኛ ሰነድና የሀሰት ሪፖርት ያቀረበ፣ የምርት ውጤት መቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን ሆን ብሎ ያበላሸ፣ የድርጅቱን መዛግብት እንዲቃጠሉ ያደረገ፣ ትክክለኛ ያልሆነ ማስረጃ በማቅረብ ሥራ የተቀጠረ፣ ዕድገት/ዝውውር/ ለማግኘት የሞከረ ወይም ያገኘ ፣

8. በስራ ሰዓት ስራውን ትቶ ህገወጥ በሆነ መንገድ በመሰብሰብ አድማ ሲያካሂድ የተገኘ ፣

9. በድርጅቱ ቅጥር ግቢ በተከለከለ ቦታ ሲጋራ ሲያጨስ ወይም እሳት ሲያቀጣጥል የተገኘና ለሲጋራ መለኮሻም ለሌላ ከኤልክትሪክ እሳት ያቀጣጠለ፣

10. የተጣለበትን ሃለፊነት በመዘንጋት ጉቦ ወይም መደለያ የሰጠ ወይም የተቀበለ፣ እንዲሰጥ ወይም እንዲቀበል ያደረገ፣

11. በድርጅቱ ቅጥር ግቢ ውስጥና በሰራተኞች ሰርቪስ መኪና ላይ የተደባደበና ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ፣

12. የድርጅቱን ሰራተኛ የግል ንብረት ከሥራ ቦታ/ከግቢው/ ውስጥ የሰረቀ፣

13. የድርጅቱን ዕቃ ፣ ምርት ወይም ንብረት በአጥር ያቀበለ ፣ የሰጠና የተቀበለ ፣

14. በደርጅቱ ውስጥ ያልተፈቀደ የጦር መሳሪያ፣ ድምፅ ያለውም ሆነ የሌለው መሳሪያ፣ ተቀጣጣይ ነገር ይዞ የተገኘና ይዞ እንዲገባ የተባበረ፣

15. በድርጅቱ ውስጥ በወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘትና በጥፋትም ምክንያት ለያዘው ስራ ብቁ ወይም ታማኝ ሆኖ ያለተገኘ፤

16. የድርጅቱ ንብረት ላይ ሆን ብሎ ጉዳት ያደረሰ፣

17. ሆን ብሎ ወይም በከባድ ቸልተኝነት በስራ ቦታ ህይወትና ንብረትን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት የፈፀመ፣

18. ህግ ሲያስገድድ ወይም አሰሪው ሲጠየቅ ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ በስተቀር የጤና ምርመራ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆን

19. ስለደህንነት ጥበቃና ስለ አደጋ መከላከያ የወጡ የስራ ድንቦችን አለማክበርና አስፈላጊ የሆኑትን የአደጋ መከላከያ ጥንቃቄ ለመውሰድ ፈቃደኛ አለመሆን፣

20. በተከታታይ ለሶስት ጌዜ የስራ አፈፃፀሙ ከአጥጋቢ በታች የሆነና በዚሁ ጉዳይ ላይ በወቅቱ የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ያላስተካከለ፡፡

21. ከሰላሳ ቀናት ለሚበልጥ ጊዜ የእስራት ፍርድ ተወስኖበት ከስራ የቀረ፣

22. በድርጅቱ መሳሪያ የግል ስራውን ሲሰራ የተገኘ ጥፋቱ በሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር መምሪያ የተረጋገጠ፣

23. በሠራተኛ ማህበርና በአሠሪው ፣ በስራ ኃላፊዎች ወይም ሠራተኛው መካከል አለመግባባትና አምቧጓሮ እንዲፈጠር አሉባልት ውሸት ሲናገር የተገኘ፣

24. የድርጅቱ መገልገያ መሳሪያ እና ልዩ ልዩ ቁሳቁስ ሥራው እንደተጠናቀቀ ለድርጅቱ ሳይመልስ ለግል ሥራው እንዲውል ያደረገ ወይም ያስቀረ ወይም የለወጠ ወይም ለሌላ አሳልፎ የሰጠ፣

25. በድርጅቱ አጥር ሾልኮ የገባ ወይም የወጣ፣

26. የጥበቃ ቦታውን ጥሎ ወይም ትቶ በመሄድ የግል ሥራውን ሲሰራ የተገኘ ሠራተኛ፣

27. ከድርጀቱ የስራ ትዕዛዝ ውጭ በሥራ ሰዓትም ሆነ ውጭ በድርጅቱ ንብረት ለውጭ ሰው ወይም ድርጅት ሲሰራ ወይም ሰርቶ የተገኘ፣

28. በሥራ ሰዓት ሥራውን ትቶ ህገወጥ በሆነ መንገድ ህግና ደንብ የማይፈቅደውን ተግባር ሲፈፅም የተገኘ፣

29. በስራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት የፈጸመ ፣

30. በስራ ቦታ አካላዊ ጥቃት የፈጸመ፡፡

36.4.4 የቅጣት ማንሻ ጊዜ

1. በዚህ ህብረት ስምምነት መሰረት አንድ ሠራተኛ ቀላል ጥፋት አጥፍቶ የተገኘ ከሆነ ከተቀጣበት ቀን ጀምሮ ለስድስት ወራት ፣ ከባድ ጥፋት አጥፍቶ የተገኘ በቀጥታ ከስራ የሚያሰናብት ካልሆነ ከተቀጣበት ቀን ጀምሮ አንድ ዓመት ከሞላው የተያዘበት የቅጣት ሪከርድ እንደተሰረዘ ይቆጠራል፡፡

አንቀጽ ሰላሳ ሰባት

ሠራተኛ ስለመቀነስ

37.1 ሠራተኞች ከስራ የሚቀነሱበት አግባብ

1. የድርጅቱን አቋም ወይም የስራ እንቅስቃሴ በሚመለከት የሚከተሉት ምክንያቶች የስራ ውልን በማስጠንቀቂያ ለማቋረጥ በቂ ምክንያት ይሆናሉ፡፡

ሀ/ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 አንቀጽ 28 ተ.ቁ 3 ሠራተኞች የተሰማሩባቸው ስራዎች በከፊልም ሆነ በሙሉ በቀጥታና በዘለቄታዉ የሚያስቆም የሠራተኞች ቅነሳ የሚያስከትል ሁኔታ ሲከሰት፣

ለ/ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀፅ 18 (5) እና (6) እንደተጠበቀ ሆኖ ፋብሪካው በሚያመርታቸዉ ምርቶች ወይም በሚሰጣቸዉ አገልግሎቶች ተፈላጊነት መቀነስ ምክንያት የፋብሪካው የስራ እንቅስቃሴ በመቀዝቀዙ ወይም ትርፍ እየቀነሰ በመሄዱ የሠራተኞች ቅነሳ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በአዋጁ አንቀጽ 19 በተቀመጠው አሰራር መሰረት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

ሐ/ የፋብሪካውን ምርታማነት ለማሳደግ የአሰራር ዘዴዎችን ለመለወጥ ወይም በአዲስ ቴክኖሎጅ ለመጠቀም ሲባል የሚደረግ የሠራተኞች ቅነሳ የሚያስከትል ውሳኔ ሲኖር ፣

2. የስራ መደቡ መሠረዝ ብዙ ሠራተኞችን የሚነካ ሲሆን እና በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/20116 አንቀጽ 29(1) መሰረት የሠራተኞችን ቅነሳ የሚያስከትል ሆኖ ሲገኝ የስራ ውሉ የሚቋረጠው በዚሁ አዋጅ በአንቀጽ 29(3) የተጠቀሱት ሁኔታዎች ከተሟሉ በኋላ ነው፡፡

አንቀጽ ሰላሳ ስምንት

የስራ ውል ስለመቋረጥ ፣ የስንብት እና የአገልግሎት ካሣ ክፍያ

38.1 የስራ ውል የሚቋረጥባቸውና አገልግሎት ካሳ የሚከፈልበት ሁኔታዎች

1. ድርጅቱ በማንኛውም የሥራ መደብ ላይ የሚገኝን ሠራተኛ የሚያሰናብተው በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 ፣ በህብረት ስምምነቱ እና በዚህ መተዳደሪያ መሠረት ይሆናል፡፡

2. በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ፣ በዚህ መመሪያ እና በህብረት ስምምነቱ መሠረት በማስጠንቀቂያ ለሚቋረጡ የሥራ ውሎች የሥራ ውሉን የሚያቋርጥ ወገን አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ በጽሑፍ ይሰጣል፡፡

3. ማንኛውም ሠራተኛ በተለያየ ምክንያት የሥራ ውሉ እንዲቋረጥ ሲደረግ በሰው ኃብት ልማት አስተዳደር ጠቅላላ አገልግሎት መምሪያ የተፈረመ የሥራ ስንብት ደብዳቤ ይሰጠዋል፡፡ ስራ መሪ ከሆነ በስራ መሪዎች መተዳደሪያ ደንብ የሚታይ ይሆናል፡፡

4. በዚህ ህብረት ስምምነት በተጠቀሰው መሰረት የሚሰናበት ሠራተኛ የስንብት የአገልግሎት ካሳ ክፍያ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሰረት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

38.2 ያለማስጠንቀቂያ ወይም በዲስፕሊን ግድፈት የስራ ውል ስለማቋረጥ

በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 አንቀጽ 27 የስራ ውልን ያለማስጠንቀቂያ ማቋረጥ የሚቻልባቸው ምክንያቶች ተብለው ከተጠቀሱት መካከል አንዱን ሠራተኛው ፈጽሞ ቢገኝ የስራ ውሉ ያለማስጠንቀቂያ የሚቋረጥ ይሆናል፡፡

38.3 በስራ ችሎታ ወይም ብቃት ማነስ ምክንያት የሚደረግ ስንብት

1. የሠራተኛው የስራ ችሎታ ወይም ብቃት ማጣት ወይም ሁኔታን በሚመለከት የሚከተሉት ምክንያቶች ማስጠንቀቂያ በመስጠት የስራ ውል ለማቋራጥ የሚቻል ይሆናል፡፡

2. ሠራተኛው በፋብሪካው ውስጥ በተመሳሳይ የሥራ መደብ ላይ ካሉ ሌሎች ሠራተኞች ጋር ሲወዳደር በሥራ ውጤቱና ባለው ችሎታ ዝቅተኛ መሆኑን ሲረጋገጥ በተከታታይ በየስድስት ወር የሚሞላ የሁለት ጊዜ የሥራ አፈፃፀሙ ዝቅ ካለ ይሰናበታል፡፡ ሆኖም ይህ ከመሆኑ በፊት አስፈላጊውን የአቅም ግንባታና ስልጠና ሊሰጠው ይገባል፡፡

3. ሠራተኛው በደረሰበት የጤንነት መታወክ ወይም በአካል ጉዳት ምክንያት በስራ ውሉ የተጣለበትን ግዴታ ወይም ለተመደበበት የሥራ መደብ ለመፈጸም ወይም ለዘለቄታው ለሥራው ብቁ አለመሆኑ በሐኪሞች ሲረጋገጥ ከሥራ ይሰናበታል፡፡

38.4 በሠራተኛው አነሳሸነት ወይም በገዛ ፈቃድ የስራ ውል ማቋረጥ

1. ማንኛውም በድርጅቱ ውስጥ በቋሚ ሠራተኛነት በመስራት ላይ የሚገኝ ሠራተኛ ከድርጅቱ ጋር ያለውን ውል ማቋረጥ ቢፈልግ ለድርጅቱ የአንድ ወር ቅድመ ማስጠንቀቂያ በጽሁፍ በመስጠት ሥራውን በራሱ ፈቃድ መልቀቅ ይችላል፡፡

2. የቅድመ ማስጠንቀቂያው መቆጠር የሚጀምረው ሠራተኛው በጽሁፍ ካሳወቀበት ቀጥሎ ካለው ቀን ጀምሮ ይሆናል፡፡

3. የአንድ ወር ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሠጠ ሠራተኛ በህብረት ስምምነት ወይም ከአሠሪው ጋር በተደረገ ስምምነት በሌላ አሰራር ካልተወሰነ በስተቀር በዚሁ ጊዜ ውስጥ በስራ ውሉ የተጠቀሱ ስራዎችን እየሰራ ወይም በስራው ላይ እየተገኘ መጨረስ ይኖርበታል፡፡

38.5 በሠራተኛው አነሳሽነት ወይም በገዛ ፈቃድ የስራ ውል ማቋረጥ አፈጻጸም

1. ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የሚለቁ ሠራተኞች የመልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ሥራ የሚለቁበትን ምክንያትና ጊዜ በመጥቀስ ለሰው ኃብት ልማት አስ/ጠቅ/አገ/መምሪያ ወይም ለድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ስንብቱ እንዲፈቀድላቸው መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይሁን እንጅ የሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎችና የሰው ኃብት ልማት አስ/ጠቅ/አገ/መምሪያ በገዛ ፈቃድ የሚለቁ ሠራተኞች ጥቄያቸዉን እንዲያነሱ ሊያግባቡቧቸዉና ሊያነጋግሯቸዉ ይገባል፡፡

2. መልቀቂያ ጥያቄው የቀረበለት የስራ ኃላፊም በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ 1156/2011 እና በዚህ ህብረት ስምምነት መሠረት ስንብቱ እንዲፈጸም ማመልከቻውን ሠራተኛው ለሚሰራበት ወይም ለሚመለከተው የስራ ክፍል ይመራዋል፡፡

3. የድርጅቱ የሠው ኃብት ልማት አስ/ጠቅ/አገ/ዋና ክፍልም በመልቀቅ ሂደት ላይ የሚገኘውን ሠራተኛ የመውጫ ቃለ መጠይቅ (Exit Interview) እንዲሞላ ያደርጉለታል፡፡

4. ሠራተኛው ሥራ ለመልቀቅ የነበረውን ፍላጐት በመተው ሥራውን ለመቀጠል ሲፈልግ ሀሳቡን መለወጡን የሚገልጽ ማመልከቻ በመጻፍ ለዋና ስራ አስኪያጅ ወይም ለሰው ኃብት ልማት አስ/ጠቅ/አገ/መምሪያ ያቀርባል፡፡

5. ስራውን እንዲለቅ የተፈቀደለት ሠራተኛ ለስራ ክፍሉ ሪፖርት ያደርጋል ፣ ሠራተኛው ሥራውን ከመልቀቁ በፊት ስለሥራው ሁኔታ በእንጥልጥል ላይ ያሉ እና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን ለቅርብ ስራ ኃላፊው ወይም ለሚያስረክበዉ ሠራተኛ መግለጽ ወይም በጽሑፍ ሪፖርት በማቅረብ ማሳወቅ አለበት፡፡

6. ሠራተኛው የመልቀቅ ፍላጐቱን ካልቀየረ የሰው ኃብት ልማት አስ/ጠቅ/አገ/መምሪያ የስንብት አፈጸጸሙ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ፣ በህብረት ስምምነትና በዚህ መመሪያ መሰረት እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡

7. ሁሉም ዓይነት የክሊራንስ ፎርማሊቲዎች ሲሟሉ የሰው ኃብት ልማት አስ/ጠቅ/አገ/መምሪያ ለሠራተኛው ክሊራንስና ባለው ሕግ/መመሪያ መሠረት የሚገባውን ክፍያ እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡

38.6 የስንብት አፈጻጸም አግባቦች

1. በሠራተኛው አነሳሸነት የሥራ ውል ሲቋረጥ ድርጅቱ የሚለቀውን ሠራተኛ ቃለ መጠይቅ በማድረግ ወይም ለዚህ ተብሎ የተዘጋጀ መጠይቅ እንዲሞላ በማድረግ ወደፊት በፋብሪካው ውስጥ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ሁኔታዎች ለማሻሻል ይጠቀምበታል፡፡

2. በማንኛውም ምክንያት ከድርጅቱ የተሰናበተ ሠራተኛ የስንብት ደብዳቤ እና ሌሎች ከድርጅቱ የሚገባው ጥቅም ከመውሰዱ በፊት የተረከበውን ንብረት ማስረከብ ፣ መታወቂያ መመለስና ከማንኛውም ዕዳ ነፃ ስለመሆኑ ክሊራንስ ማቅረብ አለበት፡፡

3. ከሥራ የተሰናበተ ሠራተኛ በእጁ የሚገኝ የድርጅቱን ንብረትና ሰነድ ማስረከቡ ሲረጋገጥ ሠራተኛው ሲሰራ የነበረውን የሥራ ዓይነት (ቋሚ፣ ኮንትራት…) ፣ ያገለገለበት ጊዜ ፣ ሲከፈለው የነበረው ደመወዝ ፣ የስራ መደብና የስራ ደረጃ የሚገልጽ የምስክር ወረቀት በሰው ኃብት ልማት አስ/ጠቅ/አገ/መምሪያ በኩል ይሰጠዋል፡፡

አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ

የቅሬታ አቀራረብ ሥነ -ሥርዓትና ውሳኔ አሰጣጥ

39.1 ዓላማ

ሠራተኛው የሚያነሳውን ቅሬታ ወደሶስተኛ አካል ከመውሰዱ በፊት በድርጅቱ ውስጥ ፍትሃዊና አግባብ በሆነ እንዲሁም ፈጣንና ቀልጣፋ በሆነ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት የማስቻልና ሠራተኛው ሙሉ ጊዜውንና አዕምሮውን ሥራ ላይ እንዲያውል የማድረግ ዓላማ አለው፡፡

39.2 ቅሬታ የማቅረብ መብት

ማንኛውም ሠራተኛ ህጋዊ መብቴ ተጓድሎብኛል ወይም በደል ተፈፅሞብኛል በማለት ቅር የተሰኘ እንደሆነ በዚህ መመሪያ መሠረት ቅሬታው እንዲታይለትና የመፍትሄ እርምጃ እንደወሰድለት የመጠየቅ መብት አለው፡፡ በዚሁ መሠረት፡-

  • ከህጎች ፣ አዋጅ ፣ መመሪያዎች፣ ህብረት ስምምነትና መተዳደሪያ ደንብ አተረጓጎምና አፈጻጸም፤
  • ከመብቶችና ጥቅማ ጥቅሞች አጠባበቅ፤
  • ከሥራ አካባቢ ጤንነትና ደህንነት ሁኔታዎች፤
  • ከሥራ ምደባና ደረጃ ፣ የደረጃ ዕድገት አሰጣጥ ፣ ዝውውር እና ተተኪነት አሠጣጥ፤
  • ከሥራ አፈጻጸም ምዘና ፤
  • ከሥራ ኃላፊዎች ከሚፈፀሙ ተገቢ ያልሆኑ ተፅዕኖዎች ፤
  • ከዲሲፕሊን እርምጃ አወሳሰድ ፤
  • ከሥራ ባልደረቦች ጋር በሚነሳ ሁከት ወይም ፣
  • የአገልግሎት ሁኔታዎችን ከሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ምክንያት በደል ደረሰብኝ የሚል ሠራተኛ ቅሬታውን ሊያቀርብ ይችላል፡፡

39.3 በየደረጃ ያለ የሥራ መሪ ኃላፊነት

1. ለቅሬታው ውሳኔ የሚሰጠው የሥራ ኃላፊ የቀረበለት ቅሬታ በቅሬታ ማቅረቢያ ቅጽ መሠረት መሆኑን በማረጋገጥ ጉዳዩን በጥንቃቄና በአግባቡ በመመርመር ተገቢውን ውሳኔ በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ መስጠት አለበት፡፡

2. በየደረጃው ያለ የሥራ መሪ ቅሬታና አለመግባባቶች እንዳይፈጠሩ አግባብ ያላቸው ሕጎች ፣ ደንቦችና መመሪያዎችና ስምምነቶችን በአግባቡ ተግባራዊ ያደርጋል፡፡

3. ቅሬታዎችና አለመግባባቶች ሲከሰቱ አግባብ ባላቸው ህጎች ፣ ደንቦች ፣ መመሪያዎችና ስምምነቶች መሠረት በማድረግ ለችግሩ መፍትሔ ይሰጣል፡፡

4. ቅሬታዎችንና አለመግባባቶችን የቅሬታ አፈታት ሂደትን መሠረት በማድረግ ለቀረበለት ቅሬታ ምላሽ ይሰጣል፡፡

5. በየደረጃው ያለ የሥራ መሪ የሚቀርብለትን ቅሬታ በጥንቃቄና በአግባቡ በመመርመር ተገቢውን ምላሽ በተገቢው ጊዜ መስጠት አለበት፡፡

6. በየደረጃው ያለ የሥራ መሪ ለቀረበለት ቅሬታ የሚሰጠው ምላሽ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ባለው ሁኔታ ግልጽ ፣ የማያሻማ ፣ ፍትሃዊና አድልዎ በሌለበት ሁኔታ ምላሽ ሊያቀርብ ይገባል፡፡

7. ለቅሬታው ውሳኔን የሚሰጠው አካል ውሳኔውን በጽሑፍ ወይም በተዘጋጀው ቅጽ ላይ ማድረግ ይገባዋል፡፡

39.4 የቅሬታ አቅራቢ ሠራተኛ ኃላፊነት

1. ማንኛውም የፋብሪካው ሠራተኛ ቅሬታ ሲኖረው በዚህ መመሪያ ቅሬታ አቀራረብ ፣ በሕብረት ስምምነት አቤቱታውን ማቅረብ አለበት፡፡

2. ቅሬታን ለማቅረብ ሠራተኛው በአካል ወይም የሰራተኛ ማህበር አባል ከሆነ በማህበሩ በኩል ማቅረብ ይችላል፡፡

3. ቅሬታውን ለማቅረብ ከመደበኛ ሥራው የሚለይ ሠራተኛ ሥራ በማይበደልበት ሁኔታ ከቅርብ የሥራ ኃላፊው ፈቃድ ማግኘት አለበት፡፡

39.5 የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ኃላፊነት

የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ የሚከተሉት ተግባርና ኃላፊነቶች ይኖሩታል፡-

1. ማንኛውም የድርጅቱ ሠራተኛ ይህን መመሪያ ተከትሎ ቅሬታውን ሲያቀርብለት ወይም ለፋብሪካው የበላይ ኃላፊ ለአስቸኳይ ማጣራት የሚመሩለትን ጉዳዮች በማጣራትና በመመርመር ውጤቱን በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለመራለት አካል የማቅረብ ኃላፊነት አለበት፡፡

2. ኮሚቴው ቅሬታ ያቀረበውን ወገን አስጠርቶ የማነጋገር ፣ ለቅሬታው በማስረጃነት የቀረቡትን ሰነዶች እንደ አስፈላጊነቱም ተጨማሪ ሰነዶችን ከሥራ ክፍሎች በመጠየቅና በማግኘት ጉዳዩን የመመርመርና የማጣራት መብት አለው፡፡

3. ኮሚቴው ቅሬታ አቅራቢው ካቀረባቸው ቅሬታዎች ጋር ግንኙነት አላቸው የሚላቸውን የድርጅቱን የሥራ ኃላፊዎች ወይም ሠራተኛን የማነጋገርና የማጣራት ኃላፊነት አለበት፡፡

4. ኮሚቴው የሚያቀርበው የመፍትሔ ሃሳብ ግልጽ ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ባለው ሁኔታ ፍትሃዊና ከአድልዎ ነጻ በሆነ አግባብ ህብረት ስምምነትን ፣ ህጎች ፣ መመሪያዎች እና ደንቦች መሠረት ያደረገ ሊሆን ይገባል፡፡

5. ኮሚቴው በቀረቡት ቅሬታዎች ዙሪያ ለማጣራትና ለመመርመር እንዲያስችለው ሰነዶችን እና መረጃዎችን ለማቅረብ ፈቃደኛ ያልሆነ የሥራ ኃላፊ ቢገኝ ጉዳዩን ለሚመለከተው የስራ ኃላፊ ሪፖርት ያደርጋል ወይም ያሳውቃል፡፡

39.6 የቅሬታ ማቅረቢያ የጊዜ ገደብ

1. ቅሬታ ያለው ሠራተኛ የቅሬታ ምክንያት የሆነው ሰነድ በደረሰው ወይም በተፈጸመ በአምስት ተከታታይ የሥራ ቀናት ጊዜ ውስጥ ቅሬታውን ደብዳቤውን ወይም ለቅሬታ ምንጭ የሆነውን ጉዳይ ለወሰነው አካል ማቅረብ አለበት፡፡

2. ለቅሬታው በቂና አጥጋቢ ምላሽ አልተሰጠኝም ብሎ የሚያስብ ከሆነ ቀጥሎ ለሚገኘው ስራ ኃላፊ በአምስት ቀናት ውስጥ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ አሁንም ምላሹ ካላረካው ለዋና ስራ አስኪያጅ በአምስት ቀናት ውስጥ ያቀርባል፡፡ ዋና ስራ አስኪያጅ ጉዳዩ በቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ተጣርቶ እንዲቀርብ ሊመራው ወይም ውሳኔ ሊሰጥበት ይችላል፡፡

3. የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ ቅሬታውን እንዲያጣራ በደረሰው በአስር ተከታታይ የስራ ቀናት ውስጥ ጉዳዩን መርምሮና አጣርቶ መመሪያውን ላስተላለፈው አካል የውሳኔ ሀሳቡን ያቀርባል፡፡

4. ከኮሚቴው የውሳኔ ሀሳብ የደረሰው ዋና ስራ አስኪያጅ ሰነዱ በደረሰው በአምስት ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ ውሳኔውን ይሰጣል፡፡

5. በዚህ መመሪያ ከተጠቀሰው የቅሬታ ማቅረቢያ ጊዜ ገደብ ውጪ የሚቀርቡ ቅሬታዎች ተቀባይነት የላቸውም፡፡

6. በዚህ አንቀጽ ተ.ቁ 1-5 የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ቅሬታውን ሊያቀርብ ያልቻለ ቅሬታ አቅራቢ ከአቅም በላይ የሆነበትን ጉዳይ ማስረጃ ያቀረበ ከሆነ ቅሬታውን የሚያቀርብበት ጊዜ እስከ አምስት ተከታታይ የሥራ ቀናት ሊራዘምለት ይችላል፡፡

39.7 የቅሬታ ማመልከቻ

ቅሬታው እንዲሰማለት የሚፈልግ ሠራተኛ የተዘጋጀውን ማመልከቻ የሚከተሉትን ነጥቦች በማካተት ሞልቶና ተጨማሪ የሚላቸውን ማስረጃዎች አባሪ በማድረግ ያቀርባል፡፡

  • የአመልካች ስም ከነአያት እና መለያ ቁጥሩ ፣
  • የሚሰራበት የሥራ ቦታና የሥራ ክፍል ፣
  • የቅርብ አለቃው ስም፣
  • የቅሬታ መንስኤ፣
  • ደጋፊ ማስረጃዎች፣
  • አመልካቹ የሚሻው መፍትሔ፣
  • ቀንና ፊርማ ፣

39.8 የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ስለማቋቋም

በድርጅቱ በዋና ሥራ አስኪያጅ የሠራተኞችን ቅሬታ የሚያጣራ ኮሚቴ ሊቋቋም ይችላል፡፡

39.9 የቅሬታ ኮሚቴ አባላት መመዘኛ

1. በግልጽነት ፣ ተነሳሽነትና በባለቤትነት ስሜት የድርጅቱን ራዕይ ለማስፈጸም ቁርጠኛ የሆነ ፣ በመልካም ሥነ-ምግባርና በሥራ አፈጻጸሙ የተመሰገነ፡፡

2. ባለፉት አስራ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በከባድ ዲሲፕሊን ጉድለት ያልተቀጣ፡፡

3. የተቋሙን ሁኔታ በጥልቀት የሚያውቅ፡፡

39.10 የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት አመዳደብ

1. የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ እንደአስፈላጊነቱ በዋና ስራ አስኪያጅ የሚመደቡ ይሆናል፡፡

2. የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባላት ቁጥር እንደጉዳዩ ስፋትና ውስብስብነት የሚወሰን ሆኖ ከሶስት እስከ አምስት አባላት ይኖሩታል፡፡

3. በቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ድምጽ የሚሰጥ አንድ የሠራተኛ ማህበር ተወካይ በአባልነት የሚካተት ይሆናል፡፡

39.11 የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ ምልዓተ ጉባኤና የድምፅ አሰጣጥ

1. የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው ለሥራው ባስፈለገ ጊዜ በማናቸውም ጊዜ ሊሰበሰብ ይችላል፡፡

2. በኮሚቴው ስብሰባ ላይ አምስት አባላት ላሉት ኮሚቴ ሰብሳቢውና ሌሎች ሁለት አባላት ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ ይሆናል፡፡ ኮሚቴው ሶስት አባላት ብቻ ያሉት ከሆኑ ግን ሶስቱም መገኘት ወይም ባልተገኙት ላይ መተካት አለበት፡፡

3. ኮሚቴው የሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ የሚያልፈው በድምፅ ብልጫ ይሆናል፡፡ ድምፁ እኩል ለእኩል የተከፈለ እንደሆነ ሰብሳቢው ያለበት ወገን ያቀረበው ሀሳብ ያልፋል፡፡ በሃሳብ የተለየ አባል የተለየበትን ምክንያት በጽሁፍ በግልፅ በማስፈር ቃለ ጉባኤው ላይ መፈረም አለበት፡፡

39.12 የኮሚቴ አባላትን ስለመሰረዝና ከስብሰባ ስለመነሳት

1. ማንኛውም የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባል ቅሬታ ካቀረበ ሠራተኛ ጋር ፀብ ፣ የሥጋ ወይም የጋብቻ ዝምድና ያለው መሆኑ ሲረጋገጥ ለቀረበው ቅሬታ ብቻ ከስብሰባው እንዲነሳ ይደረጋል፡፡

2. ማንኛውም የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ አባል፡-

  • በኮሚቴው በመታየት ላይ ያለ ቅሬታን በሚመለከት ሚስጥር ያባከነ ፣
  • የኮሚቴውን ሥራ በማናቸውም አኳኋን ያደናቀፈ ወይም በዚህ መመሪያ ለኮሚቴ አባልነት የተቀመጡ መመዘኛዎችን ያጓደለ እንደሆነ ከአባልነት ሊሰረዝ ይችላል፡፡

39.13 የቅሬታ ውሳኔ አሠጣጥ

1. የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይም የተወከለ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ በደረሰው ከአምስት የሥራ ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ኮሚቴው የወሰነውን ውሳኔ በማጽደቅ ወይም በቂ ምክንያት ሲኖረው፡-

  • በኮሚቴው የቀረበውን ሀሳብ ለመቀበል ፣
  • በቂና አሳማኝ ምክንያት ካለው የተለየ ውሳኔ ለመስጠት ፣
  • ኮሚቴው ጉዳዩን እንደገና እንዲመረምር ለማዘዝ ይችላል፡፡

2. በዚህ መሠረት የተሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ በመሆን ለቅሬታ አቅራቢው በጽሁፍ እንዲደርሰው ይደረጋል፡፡

አንቀጽ አርባ

ጡረታ ለሚወጡ ሠራተኞች

40.1 ማንኛውም በድርጅቱ ውስጥ ለረዥም ጊዜ አገልግሎት የሰጠ ሠራተኛ በጡረታ ከድርጅቱ ጋር ያለው የሥራ ውል ዕድሜው ለጡረታ በመድረሱ ምክንያት በሚቋረጥበት ጊዜ በድርጅቱ በነበረው ቆይታ ላበረከተው አስተዋጽኦ ብር 5,000.00 (አምስት ሺህ ብር) ከምስክር ወረቀት ጋር ይሰጠዋል፡፡

አንቀጽ አርባ አንድ

የጋራ ግዴታና ኃላፊነት

41.1 ድርጅቱና የሰራተኛ ማህበሩ በጋራ በመተባበር ይህንን የህብረት ስምምነት በሥራ ላይ እንዲውልና ተፈፃሚነት እንዲኖረው ተገቢውን ጥረት የማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡

አንቀጽ አርባ ሁለት

የህጎች ውጤት

42.1 ይህ ህብረት ስምምነት ተመዝግቦ ሥራ ላይ ቢውልም ሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ የመንግስት ፖሊሲ ወይም ህግን የሚቃረን ዓረፍተ-ነገር፣ ቃል ወይም ሀረግ ወይም ሀሳብ በሚኖርበት ጊዜ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡

42.2 በህብረት ስምምነት ውስጥ የተጠቀሱ ወይም ያልተጠቀሱ ቢሆንም እንኳ ከዚህ ቀደም የወጡና የሚወጡ የመንግስት ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ትዕዛዞች ሁሉ በዚህ ህብረት ስምምነት አካል ሆነው ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል፡፡

አንቀጽ አርባ ሶስት

የህብረት ስምምነት አተረጓጎም

43.1 በህብረት ስምምነት ትርጎሞች ላይ የሚነሳ ማናቸውም ክርክር በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሰረት ይፈፀማል፡፡

አንቀጽ አርባ አራት

የህብረት ስምምነቱ ወሰን

44.1 ይህ ህብረት ስምምነት በድርጅቱና በመሰረታዊ ሠራተኛ ማህበር እና ሠራተኞች መካከል ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን የድርጅቱ የስራ መሪዎችን አያጠቃልልም፡፡

44.2 በዚህ ህብረት ስምምነት አንቀፆች ከእያንዳንዱ ሠራተኛ የቅጥር ውል ጋር ተጨማሪ ውል ሆነው ይቆጠራሉ፡፡

አንቀጽ አርባ አምስት

የሥራ ማቆምና ስለስራ መዝጋት ፣ መቀዛቀዝ

45.1 የስራ ማቆምና ስለስራ መዝጋት በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/11 አንቀጽ 158 ፣ 159 ፣ 160 እና 161 መሰረት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

አንቀጽ አርባ ስድስት

የጋራ ምክክር

46.1 እንደአስፈላጊነቱ ሁለቱም ወገኖች የጋራ ምክክር ለማድረግ ተስማምተናል፡፡

አንቀጽ አርባ ሰባት

በሕብረት ስምምነት ስላልተጠቀሱ ጉዳዮች

47.1 በዚህ ህብረት ሥምምነት ውስጥ ያልተጠቀሱ ጉዳዮች መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበሩ እና ድርጅቱ በጋራ ተወያይተው ሲስማሙ የህብረት ስምምነቱ አካል እንዲሆን ይደረጋል፡፡

47.2 ከአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 እና ከዚህ ህብረት ስምምነት ጋር የሚቃረኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ሠራተኛ ማህበሩና ድርጅቱ በቅድሚያ ተወያይተው ከተስማሙ በኋላ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እንዲያጸድቀውና እንዲመዘገብ ይደረጋል፡፡

47.3 ይህንን ህብረት ስምምነት የሚቃረኑ በድርጅቱ የሚዘጋጁ ደንቦች ፣ መመሪያዎች ፣ ውሳኔዎችና አሰራሮች ተፈጻሚነት አይኖራቸውም፡፡

አንቀጽ አርባ ስምንት

የህብረት ስምምነቱ ፀንቶ ስለሚቆይበት

48.1 ይህ የህብረት ስምምነት በሁለቱ ወገኞች ከተፈፀመ በኋላ የስምምነቱ ቅፆች በተዋዋይ ወገኖች አማካኝነት ለሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለምዝገባ ይላካል፡፡

48.2 ይህ የህብረት ስምምነት በሁለቱ ተዋዋዮች ወገኖች ተፈርሞና ለሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቀርቦ ከተመዘገበበት ቀን አንስቶ ለሶስት አመታት የፀና ይሆናል፡፡

አባሪ

አባሪ አንድ - /የሥራ ልብስና አደጋ መከላከያ/

1. ሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር መምሪያ

ተ.ቁ የስራ መደብ የስራ ላይ አልባሳት ወይም አደጋ መከላከያ የሚሰጥበት ጊዜ
1 ለሰው ኃብት ልማትና አስተዳደር የቢሮ/ባለሙያዎች ኦቨር ኮት በዓመት አንድ ጊዜ
2 ጥበቃ ሠራተኞች (ለወንድ) ሱሪና ሸሚዝ ፣ ቆዳ ጫማ ፣ በ6 ወር አንድ ጊዜ
ካፖርት ፣ የዝናብ ልብስ በ3 ዓመት 1 ጊዜ
3 ለሴት ፈታሽ ጥበቃዎች ጉርድና ሸሚዝ ፣ ቆዳ ጫማ ፣ በ6 ወር አንድ ጊዜ
የዝናብ ልብስ በ3 አመት 1 ጊዜ
4 የመዝገብ ቤት ሠራተኛ ኦቨር ኮት በዓመት አንድ ጊዜ
5 ሰአት ቁጥጥር ኦቨር ኮት በዓመት አንድ ጊዜ
6 ተላላኪ ኦቨር ኮት ፣ ጫማ በዓመት አንድ ጊዜ
7 ጽዳት ሠራተኛ ኦቨር ኮት ፣ ቆዳ ጫማ በ6 ወር አንድ ጊዜ
ፕላስቲክ ጓንት በ3 ወር አንድ ጊዜ
ሳሙና (አጃክስና ኖራ ሳሙና) በወር አንድ ጊዜ
8 አትክልተኛ ኦቨር ኮት ፣ ጫማ (በ1ኛ 6 ወር ቆዳ ጫማ እና በ2ኛ ቦት ጫማ ) በ6 ወር አንድ ጊዜ
ፕላስቲክ ጓንት በ3 ወር አንድ ጊዜ
ሳሙና (አጃክስና ኖራ ሳሙና) በወር አንድ ጊዜ
9 ጠቅላላ አገልግሎት ሠራተኛ ኦቨር ኮት ፣ቆዳ ጫማ ፣ ኦቨር ኮት በ6 ወር ፣ ጫማ በዓመት አንድ ጊዜ
10 ጉልበት ሠራተኞች ቱታ ፣ ቆዳ ጫማ ኦቨር ኮት በ6 ወር ፣ ጫማ በዓመት አንድ ጊዜ
የጨርቅ ጓንት በወር አንድ ጊዜ

2. ግዥና ንብረት አስተዳደር መምሪያ

ተ.ቁ የስራ መደብ የስራ ላይ አልባሳት ወይም አደጋ መከላከያ የሚሰጥበት ጊዜ
1 የጥሬ ዕቃ መጋዘን ኃላፊና ሠራተኛ ኦቨር ኮት ፣ ቆዳ ጫማ ፣ በዓመት አንድ ጊዜ
2 የመለዋወጫ ዕቃ መጋዘን ኃላፊና ሠራተኛ ኦቨር ኮት ፣ ቆዳ ጫማ ፣ በዓመት አንድ ጊዜ
3 የተጠናቀቀ ምርት መጋዘን ኃላፊና ሠራተኛ ኦቨር ኮት ፣ ቆዳ ጫማ ፣ በዓመት አንድ ጊዜ
4 ግዥና ንብረት ክፍል ሠራተኛ ኦቨር ኮት ፣ በዓመት አንድ ጊዜ

3. ምርት መምሪያ

ተ.ቁ የስራ መደብ የስራ ላይ አልባሳት ወይም አደጋ መከላከያ የሚሰጥበት ጊዜ
1 ለምርት ጸሀፊ ፣ ለፈረቃ መሪ ፣ ለፎርማኖች ኦቨር ኮት በ6 ወር አንድ ጊዜ
2 ለዋይንደር ሠራተኞች ፣ ጥሬ ዕቃ ቀላቃይ ፣ ዶፈር(ክር ክፍል) ፣ሪሳይክል ፣ ላሚኔሽን ፣ ማጠናቀቂያ የስራ ክፍል ቱታ ፣ በ6 ወር አንድ ጊዜ
3 ሽመና (ሉም) ፣ ስፌት ፣ የምርት ጽዳት ኦቨር ኮት በ6 ወር አንድ ጊዜ
4 ስፌት ኦፕሬተር ፣ ህትመት ፣ የምርት ጽዳት (ስፌት ሰብሳቢ አይመለከትም) አጃክስ በወር አንድ ጊዜ
5 ሽምና(ሉም) ኦፕሬተር (ሰልጣኝ ሉም አይመለከትም) አጃክስ በየሁለት ወር አንድ ጊዜ
6 ሽመና (ሉም) ሠራተኞች አስፈላጊነቱ በሚመለከተው አካል ተጠንቶ ሲወሰን የጆሮ ድምጽ መከላከያ በ6 ወር አንድ ጊዜ
7 ለህትመት (እንደስራ ክፍል የሚሰጥ ) ፕላስቲክ ጓንት በየሁለት ወር
8 ለምርት ጽዳት ሠራተኞች ፣ ፕላስቲክ ጓንት በየሁለት ወር
9 እሸጋ ፣ ዋይንደር ፣ ሪሳይክል ፣ ላሚኔሽን ሠራተኞች የጨርቅ ጓንት በየአንድ ወሩ
10 እሸጋ የቆዳ ጫማ ጫማ በዓመት አንድ ጊዜ

4. ቴክኒክ ክፍል

ተ.ቁ የስራ መደብ የስራ ላይ አልባሳት ወይም አደጋ መከላከያ የሚሰጥበት ጊዜ
1 ለመካኒክ ኦቨር ኮትና ቱታ በ6 ወር አንድ ጊዜ
2 ለኤሌክትሪሽያን ቀይ ኦቨር ኮትና ቱታ በ6 ወር አንድ ጊዜ
3 ለሁሉም ቴክኒክ መምሪያ ሠራተኞች የሴፍቲ ጫማ በዓመት አንድ ጊዜ
4 ለሁሉም ቴክኒክ መምሪያ ሠራተኞች ሳሙና እና አጃክስ (በአንደኛው ወር ሳሙና በቀጣይ ወር አጃክስ) በየአንድ ወሩ
5 ለሁሉም ቴክኒክ መምሪያ ሠራተኞች አፍና አፍንጫ ማስክ በየወር እየተፈራረቀ
4 ለመካኒካል ጥገና ክፍል ፕላስቲክ ሽርጥ በ 3ወር 1 ጊዜና እንዳአስፈላጊነቱ
5 ለሁሉም ቴክኒክ መምሪያ ሠራተኞች የድምጽ መከላከያ በ1 አመት አንድ ጊዜ

5. ፋይናንስ ዳይሬክቶሬት

ተ.ቁ የስራ መደብ የስራ ላይ አልባሳት ወይም አደጋ መከላከያ የሚሰጥበት ጊዜ
1 ፋይናንስ ክፍል ሠራተኞች ኦቨር ኮት በዓመት አንድ ጊዜ

6. ምርት ጥራት ቁጥ/ጥና/ምር/አገልግሎት

ተ.ቁ የስራ መደብ የስራ ላይ አልባሳት ወይም አደጋ መከላከያ የሚሰጥበት ጊዜ
1 ምርት ጥራት ቁጥጥር ሠራተኞች ኦቨር ኮት በየስድስት ወር

አባሪ ሁለት - የስነ ስርአት ጉድለት እና እርምጃ አወሳሰድ ሠንጠረዥ

ተ.ቁ የጥፋት ዓይነት የመጀመሪያ ጊዜ ለሁለተኛ ጊዜ ለሶስተኛ ጊዜ ለአራተኛ ጊዜ ለአምስተኛ ጊዜ
1 ያለበቂ ምክንያት 15 ደቂቃ ዘግይቶ የደረሰ ወይም ቀድሞ የወጣ የቃል ማስጠንቀቂያ በጽሁፍ ይሰጣል የቀን ደመወዝ 1/4ኛ ቅጣት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የቀን ደመወዝ ½ ኛ ቅጣት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እና የአንድ ቀን ደመወዝ የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እና የሁለት ቀን ደመወዝ
2 ያለበቂ ምክንያት ግማሽ ቀን የቀረ ግማሽ ቀን ደመወዝ 1 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ11/2 ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ2ቀን ደመወዝ የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያና የ3 ቀን ደመወዝ
3 ያለበቂ ምክንያት አንድ ቀን የቀረ 1 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ11/2 ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ2ቀን ደመወዝ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያና የ3 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያና የ4 ቀን ደመወዝ
4 ያለበቂ ምክንያት በተከታታይ 2 ቀን የቀረ የ11/2 ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ2ቀን ደመወዝ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ3ቀን ደመወዝ ስንብት  
5 ያለበቂ ምክንያት በተከታታይ 3 ቀን የቀረ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ2ቀን ደመወዝ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ3ቀን ደመወዝ ስንብት    
6 ያለበቂ ምክንያት በተከታታይ 4 ቀን የቀረ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ3ቀን ደመወዝ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ4ቀን ደመወዝ ስንብት    
7 ያለፈቃድ ወይምያለበቂ ምክንያት የሥራ ቦታን ትቶ የሄደ /መዘዋወር የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ½ ቀን ደመወዝ ቅጣትና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ1 ቀን ደመወዝ ቅጣትና የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ2ቀን ደመወዝና ስንብት
8 ከስራ ሰዓት ውጭ ያለፈቃድና ያለበቂ ምክንያት ፋብሪካው ግቢ መግባት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ1ቀን ደመወዝ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ3ቀን ደመወዝ ስንብት    
9 በአደንዛዥ ዕፅ ወይም ስካር መንፈስ ወደ ሥራ የገባ ወይም በስራ ቦታ ይዞ የተገኘ ስንብት        
10 በስራ ቦታ ስለታምና ተቀጣጣይ ነገሮች ይዞ የተገኘ ስንብት        
11 ከደንበኛ ትዕዛዝ ውጭ አምርቶ የተገኘ ጥፋቱ በማስረጃ ሲረጋገጥ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ሆኖ በተጨማሪ እንደጥፋቱ ክብደት ከዚህ በታች በተቀመጠው መሰረት ቅጣት እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል          
11.1 ከባድ ጥፋት /የጥፋቱ ክብደት ከብር 5000.00 እና ከዚያ በላይ ከሆነ ስንብት        
11.2 ከባድ ጥፋት /የጥፋቱ ክብደት ከብር 1000.00 እስከ ብር 4999.00 ከሆነ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እና የ10 ቀን ደመወዝ ቅጣት ስንብት      
11.3 መካከለኛ/ የጥፋቱ ክብደት ከብር 301.00 እስከ ብር 1000.00 የሚደርስ/ የጽሁፍ ማስጠንቀቀቂያ እና 5 ቀን ደመወዝ ቅጣት የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቀቂያ እና 10 ቀን ደመወዝ ቅጣት ስንብት    
11.4 ቀላል/ የጥፋቱ ክብደት እስከ ብር 300.00 የሚደርስ/ የጽሁፍ ማስጠንቀቀቂያ እና 2 ቀን ደመወዝ ቅጣት የጽሁፍ ማስጠንቀቀቂያ እና 3 ቀን ደመወዝ ቅጣት የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቀቂያ እና 5 ቀን ደመወዝ ቅጣት ስንብት  
12 በሳምንት ዕረፍት ቀንና በህዝብ በዓላት ትርፍ ሰዓት እንዲሰራ ተጠይቆ ከተስማማ በኋላ መቅረት የ1 ቀን ደመወዝ የየጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ2 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ3 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያና የ4 ቀን ደመወዝና ስንብት
13 በስራ ቦታና በስራ ሰአት ላይ ፣ በሠራተኛ ሰርቪስ ትራንስፖርት ውስጥ ሆኖ የስራ ኃላፊንና ሌሎች ሠራተኞች የተሳደበ ሠራተኛ ወይም ኃላፊ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ10 ቀን ደመወዝ ስንብት      
14 በስራ ሰአትና በስራ ቦታ ሠራተኛው የስራ ኃላፊውን የደበደበ እንደሆነ ፣ የስራ ኃላፊው ሠራተኛውን የደበደበ እንደሆነ ወይም ሠራተኛው ሌላ ሠራተኛን የደበደበ ከሆነ ስንብት        
15 የተሰጠውን የሥራ ትዕዛዝ ወይም መመሪያ አለመፈፀም ፣ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ሆኖ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ3ቀን ደመወዝ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ4ቀን ደመወዝ ስንብት    
16 በተሰጠው ሥራ ላይ ስህተት ወይም ጥፋት ሲደርስ እያወቀ ለተቆጣጣሪው አለማሳወቅ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ3 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ5ቀን ደመወዝ ስንብት    
17 የስራ ተቆጣጣሪ (ፎርማን ፣ ፈረቃ መሪ እና ከዚያ በላይ የሆነ) የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነቱን ያልተወጣ እንደሆነ ወይም መውሰድ የሚገባውን እርምጃ በወቅቱ አለመውሰድ ከተረጋገጠ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ሆኖ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እና የ5 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እና 10 ቀን ደመወዝ ስንብት    
18 በማይመለከተው ሥራ ገብቶ መሳሪያዎችን ወይም ማሽኖችን ያለፈቃድ የሚነካ ፣ የሚያነሳ ወይም የሚጠቀም ፣ በድርጅቱ ንብረት ፣ ማሽን ወይም ንብረቶች ላይ በከባድ ቸልተኝነት ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ሆኖ ስንብት        
19 በማይመለከተው ሥራ ገብቶ መሳሪያዎችን ወይም ማሽኖችን ያለፈቃድ የሚነካ ፣ የሚያነሳ ወይም የሚጠቀም  ፤ በድርጅቱ ንብረት ፣ ማሽን  ወይም  ንብረቶች  ላይ በቸልተኝነት ቀላል ወይም መጠነኛ ጉዳት ያደረሰ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ሆኖ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያና የ05 ቀን ስንብት      
20 ለስራ የተሰጠውን የስራ መሳሪያ ፣ ማሽን ወይም ተሸከርካሪና ሌሎች ንብረቶች ሳይፈቀድለት ለሌላ አሳልፎ የሰጠ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ሆኖ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ02 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ04 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ05 ቀን ደመወዝ ስንብት  
21 በስራ ቦታና በስራ ሰአት የግል ስራ የሠራ ወይም ሲሰራ የተገኘ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የ03 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ05 ቀን ደመወዝ ስንብት    
22 በድርጅቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከተፈቀደለት ቦታ ውጭ የተጸዳዳ ወይም ተገቢውን ንጽህና ሳይጠብቅ የድርጅቱን ግቢ ጽዳት ያበላሸና የግቢ ጽዳት ያልጠበቀ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ05 ቀን ደመወዝ ስንብት      
23 በሚያሽከረክረው መኪና ላይ የደረሰውን ግጭት የደበቀ ሹፌር ለጠፋቱ ተጠያቂ ሆኖ የየጽሁፍ ማስጠንቀቂያና 2 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና 3 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ4 ቀን ደመወዝ የየመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ና የ5 ቀን ደመወዝ ስንብት
24 በጥበቃ ስራው ላይ በትክክል የማይፈትሽ ፣ የፍተሻ አሰራሩ መፈተሸ ያለበት ቦታ ሁሉ በሚገባ የማይፈትሽ (ከራስ ጀምሮ እስከ እግር ጫፍ ድረስ) ስራውን በአግባቡ ያልተወጣ ጥበቃ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ሆኖ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እና የ5 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እና የ10 ቀን ደመወዝ ስንብት    
25 በጥበቃ ስራው ላይ በትክክል የማይፈትሽ ፣ ከድርጅቱ ንብረት አሳልፎ በቸልተኝነት ያስወጣ ፣ ከባድ ጉዳት የሚያደርሱ ተቀጣጣይ ነገሮችን ፣ ስለታማ ነገሮችን እና አደንዛዥ ዕፆችን አሳልፎ ያስገባ ፣ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ሆኖ ስንብት        
26 በፍተሻ ጊዜና ቦታ ተፈታሾችን ወይም ባለጉዳዮችን ከሥነ-ስርዓት ውጭ የሚያጉላላ ፣ የሚሳደብ የጥበቃ ሠራተኛ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ1 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ2 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ3 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ5 ቀን ደመወዝ ስንብት
27 በኃይል ከድርጅቱ ቅጥር ግቢ ለመግባት ወይም ለመውጣት የሞከረ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ5 ቀን ደመወዝ ስንብት      
28 ድርጅቱ ያዘጋጀውን የሥራ ልብስ ሳይለብስ ስራ ላይ የተገኘ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ1 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ2 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ3 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ4 ቀን ደመወዝ ስንብት
29 ስለደህንነት ጥበቃና ስለአደጋ መከላከል የወጡ ደንቦችን አለማክበር እና የአደጋ መከላከያ በሥራ ላይ አለመጠቀም ፣ ባለመጠቀሙ ምክንያት ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ሆኖ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ03 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የ05 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የ10 ቀን ደምዝ ስንብት  
30 ማንኛውም በስሙ የተጻፉ ደብዳቤዎች ፣ የስራ አፈጻጸም ወይም ክስ ቻርጅ ላይ አልፈርምም ማለት በተከሰሰበት ጥፋት ተጨማሪ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ1 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ2 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ3 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያና የ4 ቀን ደመወዝ ስንብት
31 በሥራ ሰዓትና በስራ ቦታ ተኝቶ የተገኘ ሠራተኛ በዚህ ምክንያት ለሚደርስ ጥፋት ተጠያቂ ሆኖ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ 03 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ10 ቀን ደመወዝ ስንብት    
32 ተረኛ ሆኖ በምድብ ላይ ያልተገኘ ሾፌርኛ የጥበቃ ሰራተኛ በዚህ ምክንያት የደረሰ ጥፋት ካለ ተራርቶ ተጠያቂ ሆኖ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ5 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ ጽሁፍና የ10 ቀን ደመወዝ ስንብት    
33 ኃላፊነቱን በመሸሽ ወይም በመዘንጋት ተግባሩን በትክክል ያልተወጣ ኃላፊና ተቆጣጣሪ በዚህ ምክንያት የደረሰ ጥፋት ካለ ተጣርቶ ለጥፋቱ ተጠያቂ ሆኖ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያና የ5 ቀን ደመወዝ የመጨረሻ የጽሁፍማስጠንቀቂያና የ10 ቀን ደመወዝ ስንብት    
34 በደርጅቱ የሀሰት እና አሉታዊ ወሬን የሚያወራ ወይም የሀሰት ሪፖርት ያቀረበ ወይም የሀሰት ምስክርነት የሰጠ ጥፋተኛ መሆኑ ተረጋግጦ የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ10 ቀን ደመወዝ ስንብት      
35 የፈረቃ ሰራተኛ የሆነ ለቀያሪው ሳያስረክብ ቀድሞ የወጣ ለደረሰ ጥፋት በማስረጃ ሲረጋገጥ ተጠያቂ ሆኖ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ02 ቀን ደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ03 ቀን ደመወዝ መጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ05 ቀን ስንብት  
36 የሥራ ውጤት ባለማቋረጥ ከተወሰነው የምርት ጥራትና መጠን በታች ሲሆን ከክፍሉ በሚቀርበው ሪፖርት መሰረት በሠራተኛው ጥፋት መሆኑ ተጣርቶ ሲረጋገጥ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ01 ቀን ደመወዝ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የ03 ቀንደመወዝ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የ05 ቀን ደመወዝ የመ/ጽሁፍና የ10 ቀን ደመወዝ ስንብት
37 የዝውውር ደብዳቤ ደርሶት ወደተመደበበት ቦታ ያልሄደ (ለአምስት ቀን ስራው ላይ ካልተገኘ ስንብት ፣ በአምስት ቀኑ ውስጥ የተዛወረበት ስራው ላይ ተገኝቶ ከሰራ ያልተገኘበት በቀሪ ቅጣት ተይዞ ወደስራው እንዲገባ ይደረጋል) ስንብት        
38 በድርጅቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ህገ ወጥ ፅሁፍ የፃፈ ፓስተሮችን የለጠፈ ወይም ያለድርጅቱ አስተዳደር ፈቃድ የማስተዋቂያ ሰሌዳ የተጠቀመ ማናቸውም ወረቀት ያስፈረመ፣ የፈረመና የተባበረ፣ ሳይፈቀድ ስብሰባ የተሰበሰበ ወይም የሰበሰበ ፣ የድርጅቱ ማህተም ያለበት ማስታወቂያ የገነጠለ ስንብት        
39 የፆታ ትንኮሳ የፈፀመ በበቂ ማስረጃ ሲረጋገጥ የጽሁፍ ማስጠንቀቂና የ03 ቀን ደመወዝ መጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂና የ05 ቀን ደመወዝ ስንብት    
40 የጾታዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት የፈፀመ በበቂ ማስረጃ ሲረጋገጥ ስንብት        
41 በፋብሪካው ክልል ውስጥ የሚገኙ ዛፎችን የጨፈጨፈ ፣ የዘነጠለ ፣ ቀጥፎ የተጠቀመ ጥፋተኛ መሆኑ በማስረጃ ሲረጋገጥ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እና የ3 ቀን ደመወዝ ቅጣት የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እና የ5 ቀን ደመወዝ ቅጣት ስንብት    
42 በፋብሪካው ክልል ውስጥ የሚገኙ ዛፎችን ከስሩ የቆረጠ ፣ የነቀለ ፣ ያስወገደ ስንብት        
43 ለስርቆት ወይም ለማጭበርበር በሚያመች ሁኔታ ላልተሰራ ስራ የክፍያ ሂሳብ የጠየቀ ወይም እንደተሰራ አድርጎ ያቀረበ ወይም ያስተላለፈ ጥፋተኛ መሆኑ በማስረጃ ሲረጋገጥ ስንብት        
44 ለጥበቃ ስራ የተሰጠውን መሳሪያ ወይም ጥይት የጣለ ፣ የሸጠ ፣ ለሌሎች አሳልፎ የሰጠና ለግል ጥቅም ያዋለ እና ሲጠየቅ ማቅረብ ያልቻለ በማስረጃ ሲረጋገጥ ለጥፋቱ ተጠያቂ ሆኖ ስንብት        
45 በድርጅቱ በምርት ሂደት ውስጥ የሚሰራ እና በስራ ላይ ስልክ ይዞ እያነጋገረ ወይም ሌላ ነገሮች በስልክ እየተጠቀመ የተገኘ ሠራተኛ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የ1 ቀን ደመወዝ ቅጣት የ3 ቀን ደመወዝ ቅጣት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ5 ቀን ደመወዝ ቅጣት ስንብት
46 የአንድን ብሔር ፣ ሃይማኖት ማንነት የሚያንቋሽሽ ፣ የሚያጥላሉ ወዘተ ነገሮችን በጽሁፍ ፣ በአልባሳት ፣ በተለያዩ ምልክቶች ይዞ ወይም ለብሶ ወደፋብሪካ የመጣና ይዞ የተገኘ ሠራተኛ ስንብት        
47 ሀሰተኛ የትምህርት ፣ የስራ ልምድ ፣ የህክምና ወይም ሌሎች ማስረጃዎች ያቀረበ ጉዳዩ ተጣርቶ በወንጀል የሚጠየቀው እንዳለ ሆኖ ስራ ስንብት        
48 ሠራተኞችን በፋብሪካው ላይ አሉታዊና ሀሰተኛ ነገሮች በማውራት ለአመጽና አድማ ያነሳሳ በማስረጃ ሲረጋገጥ ስንብት        
49 የተለያዩ የፋብሪካው የምርት ጥሬ ዕቃ ፣ ምርቶችን በግንዛቤ ማነስ መቀላቀል እንደጥፋቱ ክብደትና ቅለት የሚታይ ሆኖ በማስረጃ ሲረጋገጥ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ሆኖ የ1 ቀን ደመወዝ ቅጣት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እና የ3 ቀን ደመወዝ ቅጣት የጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ5 ቀን ደመወዝ ቅጣት የመጨረሻ ጽሁፍ ማስጠንቀቂያና የ10 ቀን ደመወዝ ቅጣት ስንብት
50 የተለያዩ የፋብሪካው የምርት ጥሬ ዕቃ ፣ ምርቶችን ሆነ ብሎ በቸልተኝነት መቀላቀል እንደጥፋቱ ክብደትና ቅለት የሚታይ ሆኖ በዲስፕሊን ኮሚቴ ማስረጃ ሲረጋገጥ ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ሆኖ ስንብት        

የስነ ስርአት እርምጃ ሠንጠረዥ ማጠቃለያ

  1. ከላይ በሠንጠረዡ ከተ.ቁ 1 እስከ 3 የተገለጹ የጥፋት ዓይነቶች ከአምስተኛው ቅጣት ደረጃ በኋላ በተመሳሳይ ጥፋት ላይ የተገኘ ሠራተኛ የመጨረሻው ቅጣት እየተሰጠ የሚቀጥል ሲሆን በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 መሰረት በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ስምንት ጊዜ ከሞላ ያለማስጠንቀቂያ የሚሰናበት ይሆናል፡፡
  2. ከላይ በተቀመጠው የስነ ስርአት እርምጃ ሠንጠረዥ የቅጣት ደረጃዎች መሰረት እንደጥፋቱ ሁኔታ የተቀመጡ የስነ ስርአት እርምጃዎች ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

ETH Hifam Saeed Ali PP Bag Factory -

Start date: → Not specified
End date: → Not specified
Name industry: → Manufacturing
Name industry: → Manufacture of textiles, Manufacture of leather and related products
Public/private sector: → In the private sector
Concluded by:
Name company: →  Hifam Saeed Ali PP Bag Factory
Names trade unions: →  Hifam Saeed Ali PP Bag Factory Basic Workers Association

TRAINING

Training programmes: → Yes
Apprenticeships: → No
Employer contributes to training fund for employees: → Yes

SICKNESS AND DISABILITY

Maximum for sickness pay (for 6 months): → 100 %
Maximum days for paid sickness leave: → 180 days
Provisions regarding return to work after long-term illness, e.g. cancer treatment: → No
Paid menstruation leave: → No
Pay in case of disability due to work accident: → Yes

HEALTH AND SAFETY AND MEDICAL ASSISTANCE

Medical assistance agreed: → Yes
Medical assistance for relatives agreed: → No
Contribution to health insurance agreed: → Yes
Health insurance for relatives agreed: → No
Health and safety policy agreed: → Yes
Health and safety training agreed: → No
Protective clothing provided: → Yes
Regular or yearly medical checkup or visits provided by the employer: → No
Monitoring of musculoskeletal solicitation of workstations, professional risks and/or relationship between work and health: → No clear provision
Funeral assistance: → Yes
Minimum company contribution to funeral/burial expenses: → ETB 6000.0

WORK AND FAMILY ARRANGEMENTS

Maternity paid leave: → 17 weeks
Job security after maternity leave: → No
Prohibition of discrimination related to maternity: → No
Prohibition to oblige pregnant or breastfeeding workers to perform dangerous or unhealthy work: → No
Workplace risk assessment on the safety and health of pregnant or nursing women: → No
Availability of alternatives to dangerous or unhealthy work for pregnant or breastfeeding workers: → Yes
Time off for prenatal medical examinations: → Yes
Prohibition of screening for pregnancy before regularising non-standard workers: → No
Prohibition of screening for pregnancy before promotion: → No
Facilities for nursing mothers: → No
Employer-provided childcare facilities: → No
Employer-subsidized childcare facilities: → No
Monetary tuition/subsidy for children's education: → No
Paternity paid leave: → 3 days
Leave duration in days in case of death of a relative: → 3 days

GENDER EQUALITY ISSUES

Equal pay for work of equal value: → No
Discrimination at work clauses: → Yes
Equal opportunities for promotion for women: → No
Equal opportunities for training and retraining for women: → No
Gender equality trade union officer at the workplace: → No
Clauses on sexual harassment at work: → Yes
Clauses on violence at work: → Yes
Special leave for workers subjected to domestic or intimate partner violence: → No
Support for women workers with disabilities: → No
Gender equality monitoring: → No

EMPLOYMENT CONTRACTS

Trial period duration: → 60 days
Part-time workers excluded from any provision: → No
Provisions about temporary workers: → No
Apprentices excluded from any provision: → No
Minijobs/student jobs excluded from any provision: → No

WORKING HOURS, SCHEDULES AND HOLIDAYS

Working hours per day: → 8.0
Working hours per week: → 48.0
Paid annual leave: → 16.0 days
Paid annual leave: → 3.2 weeks
Rest period of at least one day per week agreed: → Yes
Paid leave to attend court or for administrative duties: → -9.0 days
Provisions on flexible work arrangements: → No

WAGES

Wages determined by means of pay scales: → No
Adjustment for rising costs of living: → 

Meal vouchers

Meal allowances provided: → No
Free legal assistance: → No
Loading...